ጥቅምት 25/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የመካከለኛ መስመር ዝርጋታ አቅሙን ለማሳደግ ከፈረንሣዩ 'ኤሊክቲሪሲቲ ደ ፍራንስ' (EDF) ጋር በቴክኒክ እና ሥልጠና ድጋፍ ዙርያ ስምምነት ተፈራርሟል።

በኢትዮጵያ እና በአውሮፓ ኅብረት መካከል የኢኮኖሚ ትብብርን ለማጠናከር፣ አዳዲስ የኢንቨስትመንት አማራጮችን ለማስተዋወቅ እና አማራጭ የፋይናንስ ድጋፍ ዘርፎችን ለመለየት የተዘጋጀው ፎረም በትናንትናው ዕለት በፈረንሳይ ዋና ከተማ ፓሪስ መካሄድ ጀምሯል።

Post image

ፎረሙ በፈረንሳይ ትልቁ የቢዝነስ ፌዴሬሽን በሆነው ሜዴፍ አለም ዓቀፍ (MEDEF International) ከአውሮፓ ኮሚሽን ጋር በመተባበር የተዘጋጀ ሲሆን፤ በአራት ስትራቴጂካዊ ዘርፎች ማለትም በአቪዬሽን፣ ታዳሽ ሃይል፣ ትራንስፖርት እና ዲጂታል ዘርፎች ዙሪያ ያሉ አዳዲስ የኢንቨስትመንት ዕድሎች ላይ አተኩሮ በመካሄድ ላይ ይገኛል።

በዚህም ፎረም ላይ የኢትዮጵያን ልዑካን ቡድን የመሩት የኢፌዴሪ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) እንዲሁም፤ የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሺዴ የመክፈቻ ንግግር አድርገዋል፡፡

Post image

በፎረሙ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ፣ የኢንደስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን እንዲሁም፤ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ኃላፊዎችን ጨምሮ ከ100 በላይ የሚሆኑ ታዋቂ የአውሮፓ ኩባንያዎች እና የልማት ፋይናንስ ተቋማት እየተሳተፉ ይገኛሉ።

በዚህም መድረክ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ከ'ኤሊክቲሪሲቲ ደ ፍራንስ' (EDF) ጋር በቴክኒክ እና ሥልጠና ድጋፍ ዙርያ ስምምነት ያደረጉ ሲሆን፤ አጋርነቱ በኢትዮጵያ ዘመናዊ፣ ደህንነቱ የተጠበቀ እና የደንበኛን ፍላጎት ያማከለ የሃይል ማከፋፈያ ኔትወርክ አቅም ለመፍጠር ለተጀመረው ጉዞ ትልቅ ምዕራፍ ነው ተብሏል።

Post image

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ጌቱ ገረመው (ኢ/ር)፤ ፊርማውን በተመለከተ በሰጡት መግለጫ፤ አጋርነቱ የቴክኒክ አቅማችንን በማጠናከር፣ ደኅንነቱ የተጠበቀ እና አስተማማኝ የኔትወርክ ጥገናን በማረጋገጥ የኢትዮጵያን የኃይል ዘርፍ የዘመናዊነት ጉዞ ይበልጥ ወደፊት የሚያራምድ ነው ብለዋል።

በቀጣይም ባንድነት ቀልጣፋ እና ደንበኛ ተኮር የኤሌክትሪክ አገልግሎት መስጫ መሠረት የማኖር ጉዟችን ይቀጥላል ሲሉ መናገራቸውን ከአገልግሎቱ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ