ጥቅምት 25/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) በፌደራል መንግሥቱ እና በምርጫ ቦርድ ሕጋዊ ሰውነቱ በተሰረዘውን ህወሓት መካከል ያልተፈታው ችግር፤ የትግራይ ሕዝብን በተለያዩ መንገዶች እየጎዳ በመሆኑ መቆሞ አለበት ሲሉ በክልሉ የሚንቀሳቀሱ የፓለቲካ ፓርቲዎች ጠይቀዋል።
የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ተፈጻሚ አለመሆን በተመለከተ፤ የፌደራል መንግሥት ህወሓትን ተጠያቂ ሲያደርግ ህወሓት በበኩሉ የፌደራል መንግሥቱን ተጠያቂ ያደርጋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በሕዝብ ተከታዮች ምክር ቤት ቀርበው በሰጡት ማብራሪያ 'የፕሪቶሪያ ስምምነት አካል የሆነው ትጥቅ ማስፈታትን ጨምሮ የተደረሱ ስምምነቶች አለመፈጸማቸው'ን አንስተው፤ "በክልሉ ዳግም ጦርነት አያስፈልግም" ማለታቸውም ይታወሳል።
"በፕሪቶሪያ የተደረሱ ስምምነቶች ተፈጻሚ ካልሆኑ በክልሉ ዘላቂ ሰላምን ማምጣት አይቻልም በማለት ስንወተውት ቆይተናል" የሚሉት፤ የውድብ ናፅነት ትግራይ ፓርቲ ሊቀመንበር ደጀን መዝገቡ (ዶ/ር) ናቸው።
ሊቀመንበሩ ሁለቱም አካላት ለራሳቸው ፍላጎት እንጂ የሕዝቡን ችግር ለመፍታት የሚያደርጉት ጥረት ባለመኖሩ፤ በተለይም ተፈናቃዮች ችግር ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በዚህም "ዋናው የተፈናቃዮች እና የሕዝቡ ጉዳይ ተረስቶ 'ስምምነቱ በማን መካከል ተደረገ?' የሚለው ትኩረት ተደርጎበታል" ብለዋል።
የትግራይን ህዝብ ከህወሓት ነጥሎ ማየት ያስፈልጋል ያሉም ሲሆን፤ ስለሆነም "ችግር ውስጥ የሚገኘው ሕዝብ ለመታደግ እርስ በእርስ መካከሳሰቸውን በማቆም ፓለቲካዊ ችግሮቻቸውን መፍታት አለባቸው" ሲሉ ገልጸዋል።
በትግራይ ክልል ያለው ችግር ለመፍታት የፌደራል መንግሥት ሕገ-መንግሥቱና ስርዓቱ በሚፈቅደው መልኩ እንጂ ጣልቃ መግባት የለበትም ያሉት ደግሞ፤ የሳልሳይ ወያነ ትግራይ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ብርሃን አፅብሀ ናቸው።
ህወሓት በክልሉ ካሉ የፓለቲካ ኃይሎች ጋር መወያየት እና የፌደራል መንግሥት በስምምነቱ መሠረት ኃላፊነቱን መወጣት ከቻለ፤ ህወሓት እንደ ምክንያት የሚያቀርበው ችግር አይኖርም ባይ ናቸው።
በፕሪቶሪያ በተደረገው ስምምነት አደራዳሪ ወደነበሩ አካላት በመቅረብ፤ 'ከሁለቱም አካላት ምን ተግባራት ተፈጻሚ አልተደረጉም?' የሚለውን በመገምገም ውይይት ማድረግ ይጠበቃል ሲሉም ገልጸዋል።
የፌደራል መንግሥት ሆነ ህወሓት ከፓለቲካዊ ሽኩቻ ለትግራይ ሕዝብ የሚተርፍ በመሆኑ መፍትሔ ሊሰጡት ይገባል ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ "ውጊያ ይበቃል ተባብረን ሀገር እናልማ" ሲሉ መልዕክታቸውን ማስተላለፉቸው የሚታወስ ሲሆን፤ መንግሥት በትግራይ ክልል ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ዝግጁ መሆኑ በማንሳት፣ በትግራይ ክልል ያሉ አካላት ዝግጁ መሆን እንደሚጠበቅባቸው መግለጻቸውም አይዘነጋም።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
የፌደራል መንግሥትና ህወሓት ችግር የትግራይን ሕዝብ እየጎዳ በመሆኑ መቆሞ አለበት ሲሉ በክልሉ የሚገኙ የፓለቲካ ፓርቲዎች ጠየቁ