ጥቅምት 25/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች አካባቢ ያለውን የትራፊክ ፍሰትን ለመቆጣጠር፤ ተሸከርካሪዎችን የሚቆሙ ግለሰቦች ላይ የገንዘብ ቅጣት እንደሚጣል የከተማ አስተዳደሩ ትራፊክ ማኔጅመንት ባለስልጣን ለአሐዱ አስታውቋል።
በባለስልጣኑ የትራፊክ ቁጥጥር እና ሁነት አስተዳደር ዳይሬክተር አቶ አያሌው አቲሳ በተሸከርካሪ ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት የሚያደርሱ ወላጆች በትምህርት ቤቶች አካባቢዎች ላይ ተሸከርካሪ ማቆም መከልከሉን የገለጹ ሲሆን፤ ይህም የትራፊክ መጨናነቅ እንዳይከሰት እና አከባቢውን ከትራፊክ አደጋ ለመከላከል የተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
ከፍተኛ ቁጥር ያለው ተሸከርካሪዎች በትምህርት ቤቶች አከባቢ በመኖሩ፤ ይህንን ለመቆጣጠር የተሸከርካሪ ባለንብረቶች ተሸከርካሪያቸውን ለማቆም የመኪና ማቆሚያ ወይም ፓርኪንክን እንደ አማራጭ ሊጠቀሙ እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡
አክለውም ተሸከርካሪን ደርቦ እና መንገድ ዘግተው በሚቆሙ ግለሰቦች ላይ እንደ ተከሰተው የጥፋት አይነት የመቅጫ የገንዘብ እርከን ስለመኖሩ የተናገሩ ሲሆን፤ ይህንን የተላላፉ አጥፊዎች እንደ ጥፋት አይነት በገንዘብ እንደሚቀጡ ይደረጋል ብለዋል፡፡
ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በትምህርት ቤት አካባቢ የትራፊክ መጨናነቅ እና አደጋ እንዳይከሰት የትራፊክ ፍሰቱን ሊገድቡ በሚችሉ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ተሰቶ እየተሰራበት እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡
በመሆኑም በትምህርት ቤቶች አካባቢ ተሽርካሪያቸውን ባለመቆም የትራፊክ ፍሰቱ ላይ ጫና እንዳይፈጠር ወላጆች የበኩላቸውን ሃላፊነት እንዲወጡ አሳስበዋል፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
በመዲናዋ በትምህርት ቤቶች አካባቢ ተሸከርካሪዎችን ማቆም እንደሚያስቀጣ ተገለጸ