ጥቅምት 20/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) የግብፅ ፕሬዝዳንት አብድል ፈታህ አልሲሲ፤ የኤርትራን የግዛት አንድነትና ሉዓላዊነት እንዲከበር ካይሮ ሁሉን አቀፍ ድጋፍ ታደርጋለች ሲሉ ቃል ገብተዋል።

ፕሬዝዳንቱ ይህንን ያሉት የኤርትራው አቻቸው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂን በካይሮ ተቀብለው ባነጋገሩበት ወቅት ነው።

የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በዛሬው ዕለት ለአምስት ቀን የሚቆይ ጉብኝት ለማድረግ ካይሮ ገብተዋል።

በዚህም የግብፅ ፕሬዝዳንት አብዱልፈታህ አል ሲሲ ከኤርትራው አቻቸው ጋር በካይሮ በተወያዩበት ወቅት፤ ሀገራቸው ለኤርትራ ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት እንደምትደግፍ አረጋግጠዋል።

"ግብፅ ከኤርትራ ጋር ባላት ሥር የሰደደ ስትራቴጂካዊ ግንኙነት ትኮራለች" ሲሉም አል ሲሲ በውይይታቸው ተናግረዋል።

"በተለያዩ መስኮች በተለይም በኢኮኖሚ እና በኢንቨስትመንት ዘርፎች የሁለትዮሽ ትብብርን ለማጠናከር" ያላቸውን ፍላጎትም አጽንኦት መስጠታቸውን አናዶሎ ዘግቧል።

ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቄ በበኩላቸው፤ "ግብፅ በአፍሪካ ቀንድና በምስራቅ አፍሪካ ቀጠና መረጋጋትን በማጠናከር እና የልማት ጥረቶችን ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ የሁለቱ ሀገራት ዲፕሎማሲያው ትብብር ጥልቅ ጠቀሜታ አለው" ሲሉ ተደምጠዋል።

የኤርትራ ፕሬዝዳንት ይህ የግብፅ የአምስት ቀን ጉብኝት እቅድ፤ ኢትዮጵያ የአሰብ የ'ይገባኛል' ጥያቄ በተደጋጋሚ እያነሳች ባለችበት በአሁኑ ወቅት መሆኑ፤ በምስራቅ አፍሪካ ውጥረቱን ሊያባብሰው እንደሚችል አመላካች ጂኦ ፖለቲካ እንቅስቃሴዎች ታይተዋል።

ባለፈው ማክሰኞ ዕለት የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው በሰጡት ማብራሪያ፤ ከኤርትራ ጋር በአሰብ ጉዳይ ዓለም አቀፍ ሽምግልና እንዲደረግ ጠይቀዋል።

ኤርትራ በ1991 ከኢትዮጵያ ነፃነቷን አግኝታ መገንጠሏ፤ ኢትዮጵያን ወደብ አልባ አድርጓት ከ30 ዓመት በላይ ሆኗል።

በዚህ ጉዳይ ላይ የኢትዮጵያ መንግሥት "ኢትዮጵያ የወደብ መተንፈሻ አጥታ ተዘግታ አትቀጥልም" የሚል አቋም ይዞ የቀጠለ ሲሆን፤ ጉዳዩንም በርካታ ምሁራኖች ድጋፍ እየሰጡት ይገኛል።

በዚህም ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር የፖለቲካ ውጥረት ውስጥ ባለችበት በአሁኑ ወቅት፤ ታሪካዊ የኢትዮጵያ ጠላት የሆነችው ግብፅ "ለኤርትራ ግዛትና ሉዓላዊነት ድጋፍ እሰጣለሁ" ስትል በዛሬው ዕለት ለአስመራ መንግሥት ቃል ገብታለች።

በአል ሲሲ እና በኢሳያስ መካከል የተካሄደው ዉይይት ቀጠናዊ ጉዳዮችን የዳሰሰ ሲሆን፤ በሱዳን እየተካሄደ ስላለው ጦርነትም ተመልክቷል።

ሁለቱም መሪዎች በሱዳን ባለው ጦርነት ላይ ያላቸው አቋም ተመሳሳይ መሆኑን የገለጹ ሲሆን፤ ብሔራዊ መንግሥታዊ ተቋማቱን ወይም የሱዳን ጦር ኃይሎችን ለመመደገፍ ቃል ገብተዋል።

ነገር ግን በጀነራል ሃምዳን ደጋሎ ወይም ሂሜቲ የሚመራዉን የትይዩ መንግሥት እንደማይቀበሉት አረጋግጠዋል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ