ጥቅምት 21/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) በሳማርካንድ፣ ኡዝበኪስታን በ43ኛው የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) አጠቃላይ ጉባኤ ላይ በትምህርት ሚኒስትርና የብሔራዊ ዩኔስኮ ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) የተመራ የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን እየተሳተፈ ይገኛል።

ከትናንት ጥቅምት 20 በጀመረውና እስከ ሕዳር 4 ቀን 2018 ድረስ በሚካሄደው በዚህ ጉባኤ ላይ በኢትዮጵያ ባለፉት ሁለት ዓመታት በዩኔስኮ ዘርፎች የተከናወኑ ተግባራት የብሔራዊ ፓሊሲ ንግግር፤ ከፍተኛ ደረጃ ያላቸው የሀገር መሪዎች፣ መንግሥት እና ከፍተኛ የትምህርት ሚኒስትሮች የሚሳተፉበት ስብሰባ እንደሚካሄድ ይጠበቃል።
በተጨማሪም 14ኛው የወጣቶች መድረክ እንዲሁም እ.ኤ.አ. የ1972 የዓለም ቅርስ ኮንቬንሽን አባል ሀገራት 25ኛው ጠቅላላ ጉባኤ በኮንፈረንሱ የሚጠበቁ ልዩ ስብሳባዎች ናቸው።

ኢትዮጵያን ጨምሮ ሌሎች አባል ሀገራት የሚሳተፉበት በዩኔስኮ ከሦስቱ ሕጋዊ አካላት አንዱ በሆነው የሥራ አስፈፃሚ ቦርድ አባል ሀገር ሆኖ ለመመረጥ የሚካሄድ የቦርድ አባልነት ምርጫም በዚህ ጉባኤ ተጠባቂ መሆኑን አሐዱ በፈረንሳይ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ያገኘው መረጃ ያመለክታል።
የዩኔስኮ ዋና ዳይሬክተር ኦድሪ አዞላይ በጠቅላላ ጉባኤው መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ በ8 ዓመታት የሥራ ዘመናቸው ዩኔስኮ ሀብቱ ወደ 800 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ጭማሪ ማሳየቱን ገልጸው፤ ይህም የ82 በመቶ ዕድገት አለው ብለዋል።

የፋይናንስ ሕዳሴው ዩኔስኮ "በመሬት ላይ ተጨባጭ እርምጃ" የወሰደበት ስትራቴጂካዊ መልሶ ማደራጀት ምክንያት የመጣ ነው ብለዋል።
በቅርብ ዓመታት ዩኔስኮ በችግር ቀጠናዎች ላይ ከግጭት በኋላ መልሶ ግንባታ እና ሰላምን በማስፈን ረገድ ወሳኝ ሚና በመጫወት ላይ እንደሚገኝም አንስተዋል።
ዩኔስኮ በአሁኑ ጊዜ በዩክሬን፣ በየመን እና በጋዛ ትምህርትን እየደገፈ መሆኑን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፤ በሶሪያ የአሌፖ ሙዚየምን መልሶ ለማቋቋም አዲስ ተነሳሽነት መጀመሩን አስታውቀዋል።

ይህ በየሁለት ዓመቱ የሚካሄደው የዩኔስኮ አጠቃላይ ጉባኤ በትምህርት፣ ሣይንስ፣ ባሕል፣ ተግባቦት፣ መረጃና ሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ የሰላም ባሕል ለመገንባትና ዘላቂ ልማትን ለማስፈን ለአባል ሀገራት ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር ኮንፈረንስ ነው።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
 
  
  
  
 