ጥቅምት 20/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በጨርቃ ጨርቅና ፋሽን ኢንዱስትሪዎች ውስጥ ሰው ሰራሽ አስተውሎት (Artificial Intelligence) በስፋት እየተተገበረ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፤ 60 በመቶ የሚሆኑት የፋሽን ኩባንያዎች በዚሁ ቴክኖሎጂ እየታገዙ ምርቶችን ለገበያ እያቀረቡ እንደሚገኙ ተነግሯል።

ይህ የተባለው በኢትዮጵያ በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል በሚካሄደው 11ኛው የአፍሪካ ሶርሲንግ እና ፋሽን ሳምንት ላይ ነው፡፡ በዛሬው ዕለት በይፋ በተከፈተው መርሃግብር ከ20 በላይ ሀገር አቀፍ እና ዓለም አቀፍ ተቋማት በአጋርነት ተሳትፈዋል ተብሏል።

Post image

ከኢትዮጵያ በኩል የኢትዮጵያ አየር መንገድ እና የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሲሳተፉ፤ ጀርመን፣ ቻይና እና ሲንጋፖርን ጨምሮ ከተለያዩ የዓለም ሀገራት የተውጣጡ ኩባንያዎች መገኘታቸው ተገልጿል።

የድርጅቱ መስራች አቶ እስክንድር ነጋሲ ለአሐዱ እንደተናገሩት፤ ከ30 በላይ ሀገራት የተውጣጡ ከ200 በላይ አምራቾች ምርቶቻቸውን በኤግዚቢሽኑ ላይ ያቀርባሉ።

Post image

በመክፈቻ መርሃግብሩ ላይ አፍሪካ እምቅ የተፈጥሮ ሀብት ያላትና በፈጠራ የበለፀጉ ወጣቶች መገኛ እንደሆነች ተገልጿል።

የጨርቃ ጨርቅና ፋሽን ኢንዱስትሪው በአፍሪካ ውስጥ ትልቅ የሥራ ዘርፍ ሲሆን፤ 22 ሚሊዮን አፍሪካውያን በዚህ ኢንዱስትሪ ውስጥ እንደተሰማሩም ተጠቁሟል።

ይህ ዘርፍ በተለይም ለሀገር ውስጥ ፍጆታም ሆነ በኤክስፖርት በኩል ትልቅ ኢኮኖሚያዊ አስተዋፅዖ እያበረከተ መሆኑ ተገልጿል። የሰው ሰራሽ አስተውሎት (ኤአይ) ቴክኖሎጂም የጨርቃ ጨርቅና የፋሽን ኢንዱስትሪዎችን በዓለም ገበያ ተወዳዳሪነት ለማሳደግ እንደሚረዳ እምነት ተጥሎበታል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ