ጥቅምት 13/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) ግብፅ በታላቁ የሕዳሴ ግድብ አሠራር ላይ በቅርቡ ያቀረበችው "ጥንቃቄ የጎደለው አሰራር ነው" የሚል ክስ መሠረተ ቢስ እና ከእውነት የራቀ ነው ሲል የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።

ሚኒስትሩ በዛሬው ዕለት ባወጣው መግለጫ የግድቡ አሠራር በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ባገኙ የደኅንነት ደረጃዎች፣ በተረጋገጡ የውሃ ፍሰት ሞዴሎች እና በክልላዊ ትብብር መርሆዎች እንደሚመራ አጽንኦት ሰጥቶበታል ብሏል።

የግብፅ የውሃ ሀብትና መስኖ ሚኒስቴር የኢትዮጵያን እርምጃ "አንድ ወገን የወሰነው እርምጃ እና የዓለም አቀፍ ሕግ የጣሰ" ሲል በይፋ ቢከስም፤ ኢትዮጵያ ደግሞ ይህ የ'ይገባኛል' ጥያቄ እውነታውን የሚያዛባ ነው በማለት በጥብቅ ውድቅ ስታደርግ መቆየቷ ይታወሳል።

መግለጫው በማብራሪያው፤ በርካታ የውሃ ፍሰት ጥናቶች እንዳረጋገጡት የሕዳሴ ግድብ አስከፊ የጎርፍ አደጋዎችን በመከላከል፣ ግድቦች ላይ የሚከማቸውን ደለል በመቀነስና ዓመቱን ሙሉ የተረጋጋ የውሃ ፍሰትን በማረጋገጥ ለግብፅና ለሱዳን የጋራ ጥቅም አለው።

በተጨማሪም፤ ጥናቶቹ ግድቡ የውሃ አቅርቦትን በማረጋጋት በአፍሪካ ቀንድ ድርቅ የሚያስከትለውን ጉዳት ይቀንሳል ብሏል።

ኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብ ሥራ ከተጀመረበት ከ2011 ዓ.ም. ጀምሮ ከሱዳንና ከግብፅ ጋር ለመተባበር ፈቃደኛ መሆኗንና በግልጽ ማሳየቷን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በመግለጫው አስታውቋል።

ነገር ግን ካይሮ ጉዳዩን ወደ ተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ለመውሰድ ያደረገችው ተደጋጋሚ ሙከራ ቢኖርም፤ አዲስ አበባ የ"አፍሪካ ችግሮች በአፍሪካውያን መፍትሔ" በሚለው መርህ ላይ በመመሥረት የአፍሪካ ሕብረት (AU) የሚመራው ውይይት ለድርድር ትክክለኛው መድረክ መሆኑን ታምናለች" ሲል አቋሙን አሳውቋል፡፡

ከምንም በላይ ኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብፅ በታሪክ፣ በባህልና በመልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ ለዘመናት እና ለትውልድ በዓባይ ወንዝ የተሳሰሩ የጋራ እጣ ፈንታ እንዳላቸው ኢትዮጵያ ታምናለች ብሏል ሚኒስቴሩ፡፡

ስለሆነም ታላቁ የሕዳሴ ግድብ የመከፋፈል ምንጭ ሳይሆን፤ ለክልላዊ ውህደት፣ ለኃይል ትብብር እና ለጋራ ብልጽግና ማሳያ ሆኖ ነው መታየት ያለበት ሲል ገልጿል።

ኢትዮጵያ አሁንም በሱዳን እና በግብፅ ካሉ ወንድሞቿ እና እህቶቿ ጋር፤ የአባይን ወንዝ ዙሪያ በጋራ ለመስራት ዝግጁ ነች ሲልም በመግለጫው አስታውቋል፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ