ጥቅምት 13/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) የቀድሞው የሰላም ሚኒስቴር ዴኤታ አቶ ታዬ ደንደአ በዛሬው ዕለት በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አንደኛ የሽብር እና ሕገ-መንግሥታዊ ጉዳዮች ችሎት ቀርበዋል፡፡

መዝገቡ ለዛሬ ፍርድ ለመስጠ የተቀጠረ እንደነበር እና ለቀጣይ ጥቅምት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ዳግመኛ መቀጠሩን የአቶ ታዬ ጠበቃ አቶ አበራ ንጉስ ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡

ጠበቃው በችሎት ውሎው ለፍርድ ቤቱ "ቀጠሮ ለምን ይራዘማል? በቂ የምርመራ ጊዜ ነበር አይደል?" ሲሉ ቅሬታቸውን አቅርበዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ከሳሽ ወይንም ዐቃቤ ሕግ በችሎቱ አለመገኘቱን የገለጹት ጠበቃው፤ "በዚህም ከሳሽ ባልተገኘበት ሁኔታ ደግሞ ፋይል ማረዘም ሳይሆን ማቋረጥ ነው የሚቻለው" ብለዋል፡፡

መዝገቡ ውስብስብ ያልሆነ እና ከሌሎች የክስ መዝገቦች አንጻር ሲታይ ቀላል መሆኑን በመግለጽም፤ "በተለይ በሁለት ጉዳዮች ብቻ ነው ምርመራ የሚያደርገው እነሱም ከዚህ በፊት በከሳሽና ተከሳሽ የቀረቡ የሰነድና ቪድዮ ማስረጃዎችን መርምሮ ፍርድ መስጠት በመሆኑ በዛሬው ዕለት መድረስ ነበረበት" ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ይህንንም ቅሬታቸውን ለፍርድ ቤቱ ማቅረባቸውን ነው የገለጹት፡፡

የአቶ ታዬ ደንደአን የሰብዓዊ መብት አያያዝን በተመለከተ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከዚህ በፊት ለፍርድ ቤት ያቀረበውን መረጃ እና በእነሱ በኩል በተደጋጋሚ ሲቀርቡ የነበረውን ቅሬታ ምላሽ እየተሰጣቸው አለመሆኑንም ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡

በተለይ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን የካቲት 16 ቀን 2017 ዓ.ም አቶ ታዬ ደንደአ 'ደርሶባቸዋል' የተባለውን የሰብዓዊ መብጥ ጥሰት ማቅረቡን የገለጹት ጠበቃው፤ "እስከ አሁን ምላሽ ወይንም ልዩ ትዕዛዝ አለመሰጠቱ ተገቢነት የለውም" ብለዋል፡፡

አቶ ታዬ ሁከትና ብጥብጥ በማነሳሳት፣ ፀረ-ሰላም ኃይሎችን በመደገፍ እንዲሁም የጦር መሳሪያ ሕግን በመተላለፍ ተደራራቢ ወንጀሎች ተከሰው በማረሚያ ቤት ሆነው ጉዳያቸውን እየተከታተሉ እንደሚገኝ ይታወቃል።

በዛሬው የችሎት ውሎም ከሳሽ ዐቃቤ ሕግ ችሎቱ ላይ ባልተገኘበት ሁኔታ የተደረገ ክርክር በመሆኑ የክስ መዝገቡ እንዲዘጋ እና ደንበኛቸው በነጻ እንዲለቀቁ ጠበቃቸው ጥያቄ ያቀረቡ ቢሆንም፤ ጥያቄው ውድቅ ተደርጎ ለጥቅምት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ