ጥቅምት 13/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) ቦርን አጌን የአእምሮ ጤና ማገገሚያ እና የፈውስ ማዕከል የዓለም አቀፍ የአእምሮ ጤና ቀንን በማስመልከት አሐዱ ሬዲዮ እና ቴሌቭዥን ላበረከተው አስተዋጽኦ እውቅናን በመስጠት የዋንጫ ሽልማት አበርክቷል፡፡

ማዕከሉ ዓለም አቀፍ የአእምሮ ጤና ቀንን በዛሬው ዕለት በአዲስ አበባ አደዋ ሙዚየም አክብሯል፡፡

በዚህም መድረክ ላይ ማዕከሉ ላለፉት 11 ዓመታት በሚያጋጥመው ማንኛውም አይነት ችግር ዙሪያ የዜና ዘገባ በመስራት ላደረገው አስተዋጽኦ ለአሐዱ ሬዲዮ እና ቴሌቭዥን እውቅናን በመስጠት የዋንጫ ሽልማት ያበረከተ ሲሆን፤ ሽልማቱን አሐዱ ሬዲዮ ዋና ሥራ አስኪያጅ ጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠ ተቀብሏል፡፡

የማዕከሉ መስራች እና ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ ኪያ ስብሃት በዚሁ ወቅት፤ "ለረጅም ጊዜ የአእምሮ ሕሙማንን ለመርዳት በምንሰራው ሥራ የሚገጥመንን ማንኛውንም አይነት ችግር በመዘገብ ጣቢያው ያበረከተው አስተዋኦ ከፍተኛ በመሆኑ የእውቅና የሽልማቱን አበርክተናል" ሲሉ ተናግረዋል።

Post image

ማዕከሉ 120 በላይ ሕሙማንን ከጎዳና ላይ በማንሳት ከአእምሮ ሕመማቸው እንዲያገግሙ በመደገፍ ላይ እንደሚገኝ የገለጹት ወይዘሮ ኪያ፤ በዚህም 20 ሰዎች በማዕከሉ ሙሉ ለሙሉ ሕክምና አግኝተው ወደ ቤተሰባቸው እና ወደ ማህበረሰቡ መቀላቀላቀላቸውን አስታውቀዋል፡፡

"ለረጅም ጊዜ የአእምሮ ሕመም ችላ ሲባል ይስተዋላል፡፡ ነገር ግን የአእምሮ ሕመም ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ የሕመም አይነት ነው" ያሉም ሲሆን፤ የአእምሮ ጤና ችግር ሦስት አይነት ደረጃ እንዳለው ገልጸዋል፡፡

በዚህም ማዕከሉ በሦስተኛ ደረጃ ላይ የደረሱ ሕሙማንን ከጎዳና ላይ በማንሳት ከአእምሮ ሕመማቸው እንዲያገግሙ የማድረግ ሥራን እንደሚሰራ ገልጸው፤ ይህም ሥራ ለተለያዩ ድጋፍ ሰጪ ተቋማት እና ግለሰቦች ጋር በጋራ እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡

በመድረኩ የተገኙት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የማህበራዊ ዘርፍ ሚኒስቴር ድኤታ ሁሪያ አሊ፤ በሀገሪቱ የሚስተዋሉ የተለያዩ ችግሮች ለአእምሮ ሕመም አጋላጭ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

Post image

በዚህም በሀገሪቱ የሚስተዋለው ግጭት፣ ሥራ አጥነት እና የሱስ ተጋላጭነት ለአእምሮ ሕመም ችግር አጋላጭ ከሆኑ ምክንያቶች መካከል ተጠቃሽ ናቸው ብለዋል።

በመሆኑም እንደ ቦርን አጌን አይነት የግብረ ሰናይ ድርጅቶች በማበረታታት ችግሩን መቀነስ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርአያ (ፕ/ር) በበኩላቸው፤ ማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ለአእምሮ ችግር አጋላጭ እንደሆነ ተናግረዋል።

Post image

ስለሆነም የተለያዩ ተቋማት እና ግብረ ሰናይ ድርጅቶች የወጣቶች የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ላይ ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራን በስፋት ሊሰሩ ይገባል ብለዋል፡፡

ማዕከሉ በዛሬው ዕለት ባከናወነው መርሃ ግብር ከአሐዱ በተጨማሪ፤ ባለፉት 11 ዓመታት ለማዕከሉ የተለያዩ ድጋፍ ላደረጉ ተቋማት የእውቅና ሽልማት አበርክቷል።

ማዕከሉ የእውቅና ሽልማት ከሰጣቸው የመንግሥት ተቋማት መካከል፤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰላምና ፀጥታ ቢሮ፣ የደንብ ማስከበር ባለስልጣን እና የከተማ አስተዳደሩ ሥራ እና ክህሎት ቢሮ ይገኙበታል፡፡

በተጨማሪም ከኮቪድ 19 ወቅት ጀምሮ እስካሁን ድረስ በማዕከሉ ለሚገኙ ሕሙማን የእንጀራ አቅርቦት የሚያደርገው 'እማ እንጀራ' እንዲሁም፤ ታፑ የበሰለ ምግብ አቅራቢያ ድርጅት ላበረከቱት ድጋፍ የእውቅና ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ