ሰኔ 27/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ግብፅ ኢትዮጵያ በሕዳሴው ግድብ ዙሪያ ለመነጋገር የምታቀርበው ተደጋጋሚ ጥሪ ተአማኒነት የጎደለው እና ዓለም አቀፋዊ ገጽታን ለመሳብ የታለመ ነው ስትል የከሰሰች ሲሆን፤ አዲስ ውይይት እንዲጀመር የኢትዮጵያን ቅንነት እፈልጋለሁ ብላለች፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በትላንትናው ዕለት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው በሰጡት ማብራሪያ፤ የሕዳሴው ግድብ በቀጣይ መስከረም ወር ሙሉ ለሙሉ እንደሚጠናቀቅ ገልጸው፤ ግድቡ የማንንም ሉዓላዊነት የማይጎዳ መሆኑንን አረጋግጠዋል።

Post image

ነገር ግን የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላት የሆነችው ግብፅ ትላንት ምሽት በሰጠችው መግለጫ፤ "ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ በጀመረችው የግድብ ፕሮጀክት ላይ አዲስ ውይይት እንዲጀመር የኢትዮጵያን ቅንነት እፈልጋለሁ" ስትል ተማፅናለች።

የሀገሪቱ የመስኖና ቆላማ ሚኒስትር ሃኒ ሰዊላም ከውጭ ሀገር የግብፅ ዲፕሎማሲያዊ ሚሲዮኖች ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደተናገሩት፤ "አዲስ አበባ ከግብፅ እና ሱዳን ጋር ምንም አይነት አስገዳጅ ስምምነት ሳታደርግ የዓለም አቀፍ ሕግን በመጣስ ሕገ-ወጥ ግድብ እንዲጠናቀቅ ማድረጓን ቀጥላለች" ብለዋል።

ሰዊላም ኢትዮጵያ ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የምትከተለው አካሄድ ለትብብር እና አጋርነት ያለውን ቁርጠኝነት ሳይሆን "የውሃ የበላይነት አጀንዳን" የሚያንፀባርቅ ስለመሆኑ መግለጻቸውን አናዶሉ ዘግቧል።

የውሃ ሃብትና መስኖ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ፤ "ግብፅ እንዲህ አይነት የበላይነት እንዲኖር አትፈቅድም" ሲል አስታውቋል፡፡

በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የክረምቱ ወቅት ሲጠናቀቅ በፊታችን 2018 ዓ.ም መስከረም ወር ላይ የታላቁን ሕዳሴ ግድብ በይፋ ለመመረቅ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

Post image

በዚህም ኢትዮጵያ በሕዳሴው ግድብ ላይ በተደጋጋሚ የይገባኛል ጥያቄ የሚያነሱትን ግብፅና ሱዳንን የፊታችን መስከረም ወር ላይ "ታሪካዊ ክስተት" ስለሚፈጠር እንግዳ እንዲሆኑ ጥሪ አስተላልፋለች።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ግድቡ የግብፅንም ሆነ የሱዳንን ጥቅም እንደማይጎዳ አረጋግጠው፣ ፕሮጀክቱ "የቀጠናውን ትብብር ዕድልን የሚፈጥር እንጂ ግጭትን አያመጣም" በማለት ኢትዮጵያ ከግብፅ ጋር ድርድር ለመቀጠል ፍላጎት እንዳላት ገልጸዋል።

ነገር ግን ይህን የጠቅላይ ሚኒስትሩን ንግግር ያልተቀበለችው ግብፅ፤ "ኢትዮጵያ አለማቀፋዊ ገጽታዋን ለማሻሻል ያለመ የድርድር ጥሪዎችን ነው የምታቀርበው" ስትል የፕሮፓጋንዳ ክሷን አሰምታለች።

"ከ13 ዓመታት በላይ የተካሄደው የከሸፈ ድርድር” ከአዲስ አበባ የፖለቲካ ፍላጎት ማነስ ነው" ስትልም ካይሮ ወንጅላለች።

ግብፅ በግድቡ አሞላል እና ሥራ ላይ በተለይም በድርቅ ወቅት የናይል ወንዝን የውሃ ድርሻ ለመጠበቅ ሕጋዊ አስገዳጅ የሦስትዮሽ ስምምነት እንዲደረግ በተከታታይ ስትጠይቅ ቆይታለች።

ኢትዮጵያ ግድቡ ለልማትና ለመብራት ሃይል ማመንጨት አስፈላጊ እንጂ በሌሎች ሀገራት ላይ ምንም አይነት ስጋት እንደማይፈጥር በመግለጽ እነዚህን ዉንጀላዎች ውድቅ ስታደርግ ቆይታለች።

እነዚህ ተቃራኒ አመለካከቶችን ተከትሎ፤ እ.ኤ.አ በ2023 ለአጭር ጊዜ የቀጠለው ድርድር ከተቋረጠ ሦስት ዓመታትን አስቋጥሯል፡፡

ኢትዮጵያ እስካሁን ድረስ ለሕዳሴው ግድብ መሙያ ከ23 ቢሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡን ያስታወቀች ሲሆን፤ በዚህም 93 በመቶ የሚደርስ ገንዘብ በድጋፍ መልክ መሰብሰብ መቻሉ ተነግሯል፡፡

ግንባታው ሲጠናቀቅ በአፍሪካ ግዙፉ የኤሌክትሪክ ማመንጫ ግድብ እንደሚሆን የሚጠበቀው የሕዳሴ ግድብ፤ ከፍታው 145 ሜትር ሲሆን፤ ርዝመቱ ደግሞ 1 ነጥብ 8 ኪሎ ሜትር ነው።

ከ5 ቢሊዮን ዶላር በላይ ወጪ ፈሶበት ከአምስት ሺሕ በላይ ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ያመነጫል የተባለው የታላቁ ሕዳሴ ግድብ፤ ከኢትዮጵያ አልፎ ለአካባቢው ሀገራት የኤሌክትሪክ ኃይል ያቀርባል ተብሎ ይጠበቃል።

የሦስት መንግሥታት የስልጣን ዘመን ያስቆጠረው የሕዳሴው የግንባታ ፕሮጀክት አሁን ላይ 98 ነጥብ 9 በመቶ የውሃ ሙሌቱ የደረሰ ሲሆን፤ ሙሉ ለሙሉ ሊጠናቀቅ የወራት እድሜ እንደቀረው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በትላንትናው ዕለት ገልጸዋል፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ