ሰኔ 27/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 2ኛ ልዩ ስብሰባው የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ-ምግባር አዋጅን ለማሻሻል የቀረበ ረቂቅ አዋጅን መርምሮ በዝርዝር ለሚመለከተው የዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቷል።
የሚኒስትሮች ምክር ቤት ዛሬ ማለዳ ባካሄደው 48ኛ መደበኛ ስብሰባ የፌዴራል የገቢ ግብር አዋጅን ለማሻሻል የወጣ አዋጅ ላይ ተወያይቶ በሙሉ ድምጽ በማጽደቅ ወደ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ መወሰኑን አሐዱ መዘገቡ ይታወሳል፡፡
ይህንንም ተከትሎ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 2ኛ ልዩ ስብሰባውን ያካሄደ ሲሆን፤ የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ በረቂቅ አዋጁ ላይ የተዘጋጀውን አጭር ማብራሪያ አቅርበዋል፡፡

ቀደም ሲል የነበረውን አዋጅ ተከትሎ ቦርዱ ያስፈጸመው ጠቅላላ ምርጫ በሕግ ከፍተት ምክንያት የተስተዋሉ ችግሮችን እንዲሁም በፖለቲካ ፓርቲ አስተዳደር ሥራዎች ላይ ያሉ የሕግ ክፍተቶችን ለማረም የተዘጋጀ የማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ እንደሆነ አፈ ጉባኤው አስረድተዋል፡፡
የማሻሻያ አዋጁ የምርጫ ተሳታፊ ባለድርሻ አካላት ምርጫውን ሰላማዊ እና ፍትሀዊ በማድረግ ከማስፈጸም አንጻር ያላቸውን መብትና ግዴታ ለመደንገግ የወጣ ስለመሆኑም ጠቁመዋል፡፡
ረቂቅ አዋጁ ወጥነት፣ ግልጽነት እና ከህገመንግስታዊ መርሆች እና አለም አቀፍ ምርጥ ተሞክሮዎች ጋር በማጣጣም ነባሩን ህግ በማሻሻል እንደሚያጠናክርም ገልጸዋል።
ማሻሻያው ሴቶች፣ አካል ጉዳተኞች፣ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች እና ሌሎች የተገለሉ የህብረተሰብ ክፍሎች በምርጫ እና በፖለቲካ የተሻለ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ያስችላልም ተብሏል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድን ነጻነትና የአሰራር ቅልጥፍና ለማሳደግ፣ ሰፊ የፖለቲካ ተሳትፎና ተጠያቂነትን ለማስፈን የሚያስችል ማሻሻያ አዋጅ እንደሆነም አቶ ታገሰ ባቀረቡት ማብራሪያ ገልጸዋል፡፡
የምክር ቤቱ አባላት በበኩላቸው ረቂቅ አዋጁ የተመራለት ቋሚ ኮሚቴ በጥልቀት ሊያየው ይገባል ያሏቸውን ሀሳቦች አቅርበዋል፡፡
በመጨረሻም ምክር ቤቱ የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ ቁጥር 24/2017 አድርጎ ለዝርዝር እይታ ለዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በሙሉ ድምጽ መርቷል።

በተጨማሪም የሚኒስትሮች ምክር ቤት በዛሬው 48ኛ መደበኛ ስብሰባ የፌዴራል የገቢ ግብር አዋጅን ለማሻሻል የወጣ አዋጅ ላይ ተወያይቶ በሙሉ ድምጽ በማጽደቅ ወደ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ የወሰነ ሲሆን፤ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤቱ ይህን የፌዴራል የገቢ ግብር አዋጅን ለማሻሻል የቀረበ ረቂቅ አዋጅ መርምሮ በዝርዝር ለሚመለከተው የፕላን በጀትና ፋይናንስ ቋሚ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቷል፡፡
ረቂቅ አዋጁን አስመልክቶ በምክር ቤቱ የመንግሥት ረዳት ተጠሪ ሚንስትር ዴኤታ ወ/ሮ መሰረት ኃይሌ አጭር ማብራሪያ አቅርበዋል፡፡

በገቢ ግብር አዋጅ ላይ የተደረገው ማሻሻያ የኢትዮጵያን የግብር ስርአት ዘመናዊ በማድረግ የታክስ ፍትሀዊነትን ለማረጋገጥ፣ የታክስ ሕጎች እንዲከበሩ ለማድረግና የመንግስትን ገቢ ለማሳደግ የአዋጁ መሻሻል አስፈላጊ እንደሆነ ወ/ሮ መሰረት ባቀረቡት ማብራሪያ ገልጸዋል፡፡
ረቂቅ የገቢ ግብር ማሻሻያ አዋጁ ዋነኛ አላማዎች ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ ያለውን የግብር ጫና መቀነስ፣ የግብር መሰረትን ማስፋት፣ ለአነስተኛ የንግድ እንቅስቃሴዎች ቀላል የግብር አከፋፈል ስርዓት መዘርጋት፣ ለኢንቨስትመንት የሚደረገውን ጥረት ማገዝ የታክስ ማጭበርበር ጥረቶችን ለመከላከል እንዲሁም ግልጽነት በሚጎድላቸው አንቀጾች ምክንያት የሚደርሱ ውጣ ውረዶችን ማስቀረት እንደሆነ አብራርተዋል፡፡
ኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎች ከግምት ውስጥ ባስገባ ሁኔታ የግብር ስርአቱን ከዓለም ልምድ ጋር ማጣጣም የሚያስችል የማሻሻያ አዋጅ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡
በተለይም በዲጂታል ዘመን በታክስ አሰባሰብ ረገድ ሊኖር የሚችለውን ፈተና ከግምት ውስጥ በማስገባት የታክስ መሰረትን ማስፋትን እና ፍትሃዊነትን ማረጋገጥን የመሳሰሉ መንታ ግቦችን ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ተግባራዊ ማድረግ እንደሚያስችልም አስረድተዋል፡፡
የምክር ቤቱ አባላት በበኩላቸው ረቂቅ አዋጁ የሚመራለት ቋሚ ኮሚቴ በጥልቀት ሊያየው ይገባል ያሏቸውን ሀሳቦች አቅርበዋል፡፡
በመጨረሻም ምክር ቤቱ የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ ቁጥር 25/2017 አድርጎ ለዝርዝር እይታ ለፕላን በጀትና ፋይናንስ ቋሚ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በሙሉ ድምጽ መምራቱን ከምክር ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ