ሕዳር 22/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) በኢትዮጵያ ግብርናውን ሊደግፍ የሚችል የፋይናንስ አቅርቦትን የሚያጠናክር አሰራር አለመዘርጋቱ ጋርጦት የነበረውን ችግር ይፈታል የተባለ ፍኖተ ካርታ ከብሄራዊ ባንክ ጋር በመተባበር ማዘጋጀቱን ግብርና ሚኒስቴር ለአሐዱ ሬዲዮ አስታውቋል፡፡
ከዓመታት ድርድርና ውይይት በኋላ፤ ሚኒስቴሩ ይህን ፍኖተ ካርታ ለመተግበር ከብሄራዊ ባንክ ጋር ከስምምነት ላይ መድረሱን፤; በሚኒስቴሩ የገጠር ፋይናስ ክፍል ቡድን መሪና የሥራ አስፈፃሚ አባል የሆኑት አቶ ጌታቸው መኮንን ገልጸዋል፡፡
ፍኖተ ካርታው በቀጣይ በተግባር ላይ ሲውል የየፋይናንስ ሴክተሩ ያለምንም ስጋት ከላይኛው እርከን እስከ ታችኛው እርከን በሚገኘው የግብርና መዋቅር ላይ መዋለ ንዋይ ፈሰስ እንዲያደርግና፤ ኪሳራም ቢያጋጥም ከብሔራዊ ባንክ ዋስትና የሚያገኝበትን የአሰራር ስርዓት እውን ለማድረግ የሚያስችል መሆኑንም ተናግረዋል።
"ከዚህ በፊት የግልም ይሁን የመንግሥት የፋይናስ ተቋም 'የግብርናው ዘርፍ አክሳሪ ነው' ብሎ ስለሚያምን፤ መዋለ ንዋይ ለማፍሰስ ፍላጎት አልነበረውም" ሲሉ ያስታወሱት አቶ ጌታቸው፤ በአሁኑ ወቅት ግን የግብርና ሚኒስቴር ከብሔራዊ ባንክ ጋር ስምምነት በማድረግ የመጀመሪውን ፍኖተ ካርታ በመዘርጋቱ ተቋማቱ ገንዘባቸውን በግብርናው ላይ አውጥተው ኪሳራ ቢገጥማቸው ብሔራዊ ባንክ ድጎማ የሚያደርግበት ዕድል እንደሚፈጥር ጠቁመዋል።
ከ80 በመቶ በላይ የግብርና መር ኢኮኖሚ ያላት ኢትዮጵያ በአርሶ አደሮቿ ምርት ላይ ለሚደርስ አደጋ የምትሰጠው የመድኅን ሽፋን ከዜሮ በታች መሆኑን አሐዱ ግብርና ሚኒስቴርን ዋቢ አድርጎ መዘገቡ ይታወሳል፡፡
በወቅቱ እንደ ምክንያት የተነሳው የግብርናውን ዘርፍ በፋይናንስ አቅም ሊያጠናክር የሚችል ስርዓት አለመኖር እንዱና ዋነኛው ተደርጎ የተጠቀሰ ሲሆን፤ ፍኖተ ካርታው ይህንን እና ሌሎች በዘርፉ ያሉ ችግሮችን ይፈታል ተብሎ ታምኖበታል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
ግብርና ሚኒስቴር የግብርናውን ዘርፍ በፋይናንስ ለማጠናከር የሚያስችል የመጀመሪያውን ፍኖተ ካርታ ከብሔራዊ ባንክ ጋር በመተባበር ማዘጋጀቱ ተገለጸ