ሕዳር 22/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) የኢትዮጵያ አርታኢያን ማኅበር ከአንድ ዓመት በፊት በዩኔስኮ ድጋፍ ባቋቋመው "የጋዜጠኞች ደኅንነት ፓርታል" (SOJ Ethiopia) ላይ እስከአሁን የ51 ጥቃቶች ሪፖርት እንደተደረጉ አስታውቋል።

የመረጃ "ፖርታሉ" የተቋቋመው በጋዜጠኞች ላይ የደረሱ ሙያዊ ተጽዕኖዎችን፣ ክልከላዎችን፣ አፈናዎችን እንዲሁም፤ በመንግሥትም ሆነ በአሰሪዎች የሚፈጸምን አካላዊ እና ሥነ-ልቦናዊ ጥቃት በበይነ-መረብ አማካኝነት ሰብስቦ መፍትሔ ለማፈላለግ እንደሆነ ተገልጿል፡፡

የማኅበሩ ፕሮግራም አስተባባሪ ህልዳና እንዳለ እንደገለጹት ፓርታሉ የተዘጋጀው የመገናኛ ብዙኃን ደኅንነት እና ነፃነትን ለማሻሻል ሲሆን፤ በጋዜጠኞች ላይ የሚደርሱ አካላዊ እና ዲጂታል ጥቃቶችን፣ ትንኮሳዎችን እንዲሁም ጾታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶችን ለመከታተል ያለመ ነው።

በዚህም እስከአሁን በጋዜጠኞች ላይ የተፈጸሙ አካላዊ እና ሥነ-ልቦናዊ የ51 ጥቃቶች ሪፖርት ሲደረጉ፣ በሴቶች ጋዜጠኞች ላይ የሚሰነዘሩ ማስፈራሪያዎችን አስመልክቶ 13 ሪፖርቶች መቅረባቸውን ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም በእስር ላይ የሚገኙና ክስ የተመሰረተባቸው ጋዜጠኞችን አስመልክቶ ሁለት ሪፖርቶች እስካሁን መቅረባቸው ገልጸዋል፡፡

Post image

ፕሮግራም አስተባባሪዋ፤ “ጋዜጠኞች በራሳቸው ላይ የደረሰን ማንኛውንም ዓይነት ጥቃት ወይም በሌላ ባልደረባቸው ላይ ሲደርስ የተመለከቱትን ክስተት በፓርታሉ አማካኝነት ሪፖርት ያደርጋሉ። በሪፖርቱ መነሻነትም ክትትልና ምርመራ ይካሄዳል” ብለዋል።

ፓርታሉ አገልግሎቱን በሦስት ቋንቋዎች ማለትም በአማርኛ፣ ኦሮምኛ እና በእንግሊዝኛ የሚሰጥ ሲሆን፤ በቀጣይነት የፖርታሉ አገልግሎት ከኢንተርኔት ግንኙነት ውጪ እንዲሆን ጥረት እየተደረገ እንደሆነ ተገልጿል።

ከቀረቡት 51 የጥቃት ጉዳዮች ምን ያህሉ በምርመራ ሂደት ላይ እንደሚገኙ እና ምን ያህሉ እልባት እንዳገኙ፤ የማኅበሩ ፕሮግራም አስተባባሪ ከመግለጽ ተቆጥበዋል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ