ሕዳር 22/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) በአዋሽ ብሔራዊ ፓርክ ተጠልለው በብዛት ይገኙ የነበሩ እንደ የሜዳ አህያ፣ ሰጎን እና ቆርኬ ያሉ የዱር እንስሳት ዝርያዎች ከፓርኩ የመጥፋት አደጋ እንደተጋረጠባቸው የፓርኩ አስተዳደር አስታውቋል።

የፓርኩ አስተዳደር የጠፉትንና ለአደጋ የተጋለጡትን ዝርያዎች ወደ መኖሪያቸው ለመመለስ የሚያስችል ጥናት መጀመሩን ገልጿል።

Post image

የአዋሽ ብሔራዊ ፓርክ ኃላፊ አቶ አደም መሐመድ፤ የእንስሳቱ ቁጥር የተመናመነው በአየር ንብረት ለውጥ፣ በሰው ሰራሽ እና ተፈጥሯዊ አደጋዎች ምክንያቶች እንደሆነ ጠቅሰው፤ ትክክለኛ ምክንያቱን አረጋግጦ የመፍትሔ እርምጃዎችን ለመውሰድ ጥናት ተጀምሯል ብለዋል፡፡

Post image


የሌሊት ወፍ፣ አንበሳ፣ የሜዳ አህያ፣ ሰጎን እና ቆርኬን ጨምሮ 81 የአጥቢ እንስሳ ዝርያዎች በፓርኩ ተጠልለው ይኖሩ እንደነበር ከዚህ በፊት በተጠና ጥናት መረጋገጡን የተናገሩት ኃላፊው አቶ አደም መሐመድ፤ "በኢትዮጵያ ውስጥ ከተመዘገቡት ከ800 በላይ የአዋፍ ዝርያዎች መካከል ከ450 በላይ የሚሆኑት የአዋፍ ዝርያዎች በአዋሽ ብሔራዊ ፓርክ ተመዝግበዋል" ብለዋል፡፡

በተጨማሪም፤ የፓርኩ ኃላፊ በፓርኩ ውስጥ የሚገኙትን የቱሪስት መስህቦች ደኅንነት ለማስጠበቅ ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን ገልጸዋል።

Post image

በከፍተኛ የተፈጥሮ ሐብት የታደለውን፣ በርካታ እንስሳትን እና አዕዋፍን ያስጠለለውን አዋሽ ብሔራዊ ፓርክ ወደ ቀድሞ ይዞታው ለመመለስ፤ በመካሄድ ላይ ያለው ጥናት የተጀመረበት እና የሚጠናቀቅበ ጊዜ አልተጠቀሰም፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ