መስከረም 15/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) ግባችን ደህንነቱ የተጠበቀ ግልጽ እና አርአያነት ያለው የኒውክሌር መርሃ ግብር መጀመር ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ተናገሩ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሩሲያ የኑክሌር ኢንዱስትሪን 80ኛ ዓመት በዓልን ለመዘከር በሞስኮ የሚካሄደውን ዓለም አቀፍ የአቶሚክ ፎረም ላይ ለመሳተፍ ወደ ሞስኮ አቅንተዋል፡፡

ፎረሙን የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን የሚመሩት ሲሆን፤ ዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ ዳይሬክተር ራፋኤል ግሮሲ፣ የምያንማር ጊዜአዊ ፕሬዝዳንት ሚን ኡንግ፣ የቤላሩሱ ፕሬዝዳንት አሌክሳንደር ሉካሼንኮ እና የአርሜኒያው ጠቅላይ ሚኒስትር ኒኮል ፓሺያን ያሉ ዓለም አቀፍ መሪዎች በውይይቱ እየተሳተፉ ይገኛል፡፡

በመድረኩ ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ "የኢትዮጵያ ከተሞች እየዘመኑን ነው፣ ኢንደስትሪያችን እያደገ ነው፣ ኢኮኖሚያችን ከዓለም ፈጣን እድገት ከሚባሉት ተርታ ይመደባል" ብለዋል፡፡

"ነገር ግን የእኛ ምኞቶች ከፍተኛ፣ አስተማማኝ፣ ንፁህ እና የሚቀያየር ኃይል ማግኘት ነው" ያሉ ሲሆን፤ እስካሁን እየተሰራባቸው ያሉ የፀሐይ እና የነፋስ ኃይሎች ብቻቸውን እየገነባን ላለነውን ወደፊት ኃይል ማመንጨት አይችሉም" ሲሉ ተናግረዋል፡፡

"ኢትዮጵያ ከአስር ዓመታት በላይ የአረንጓዴ ሃይል ሻምፒዮን ሆና ቆይታለች" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፤ በተጨማሪም በአፍሪካ ትልቁ የሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የቁርጥናችን ምልክት ሆኖ ይቆማል ሲሉ ገልጸዋል፡፡

Post image

"ራዕያችን ከዛሬ አልፏል ሀገራችንን ወደ ፊት እያየን በሚቻለውም አቅም፤ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ፣ ዶክተሮችን አቅም ለማሳደግ፣ የውሃ አያያዝን ለመጨመር እና ሳይንቲስቶቻችንን ለኢትዮጵያ ኒውክሌር እንዲፈጥሩ ማስቻል ነው" ብለዋል፡፡

በዚህም "የኒውክሌር ኃይል ለተማሪዎቻችን እውቀትን ይከፍታል፣ ለገበሬዎች መሳሪያዎች እና ለታካሚዎች ፈውስ ያመጣል" ያሉ ሲሆን፤ እድሎች የሚበዙበት መሠረትን ማስፋት ስለመሆኑም አመላክተዋል፡፡

"ኢትዮጵያ ከፍተኛውን የደህንነት ደረጃዎች በማቀድ እና ጠንካራ የአካባቢ አቅምን በመገንባት ይህንን ኃላፊነት በጥንቃቄ ትከተላለች" ሲሉም በፎረሙ ላይ ማረጋገጫ ሰጥተዋል፡፡

"ለእኛ የኑክሌር ኃይል በኢንዱስትሪ እና በፈጠራ እንዲሁም፤ በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ዘርፍ ንቁ ተሳታፊ እንድንሆን የሚያስችል ስትራቴጂያዊ እርምጃ ነው" ሲሉም ገልጸዋል።

"በዚህ ዓመት 80 ዓመታት የኒውክሌር ኢንዱስትሪውን ያከበረውን የሩሲያ ፌዴሬሽን እውቅና ለመስጠት እፈልጋለሁ" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፤ "ሩሲያ ሳይንስ ከራዕይ ጋር ሲስማማ ምን ሊያሳካ እንደሚችላ አሳይታለች" ብለዋል፡፡

"ኢትዮጵያ ሩሲያ ያላትን እውቀት ከሰለጠነ የሰው ሃይል ጋር በማጣመር እንዲሁም፤ እያደገ ያለውን የኢትዮጵያ ገበያ በማቀናጀት ዘመናዊ የትብብር ሞዴል ለመፍጠር ተዘጋጅታለች" ሲሉም አስታውቀዋል፡፡

"እኛ ከ130 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ እያለን መጠበቅ አንችልም" በማለትም፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ተናግረዋል፡፡

"የረጅም ጊዜ ልማትን ለማረጋገጥ የኢነርጂ አቅማችንን ለማብዛት እና ኢትዮጵያውያን እምቅ አቅምን እውን ለማድረግ የኒውክሌር ኢነርጂ አስፈላጊ ነው" ሲሉም አጽንዖት ሰጥተውበታል፡፡

"ግባችን ደህንነቱ የተጠበቀ ግልጽ እና አርአያነት ያለው የኒውክሌር መርሃ ግብር መጀመር ነው" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ "ለዚህም ነው ሰላማዊ የኒውክሌር ኢነርጂ አጠቃቀምን ከዓለም አቀፍ ደረጃዎች ጋር በማጣጣም መከተልን የመረጥነው" ብለዋል፡፡

አክለውም "ኢትዮጵያ ከሩሲያ ፌዴሬሽን ጋር በጋራ በመሆን ተጨባጭ እርምጃዎችን ወስዳለች፣ የኒውክሌር መሠረተ ልማት ለመገንባት እቅድ ይዛለች፣ ባለሙያዎችን ለማሰልጠን እና ጠንካራ የቁጥጥር ማዕቀፍ ለማዘጋጀት እየሰራች ነው" ሲሉም አስታውቀዋል፡፡

በዚህም የኒውክሌር ሳይንስ የቴክኖሎጂ ማዕከል ሊቋቋም መሆኑን ያስታወቁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በሰላማዊ የኒውክሌር ሳይንስ አተገባበር ትብብር እየሰፋ መምጣቱን ገልጸዋል።

"እኛ የኑክሌር ኢነርጂ ሉዓላዊነታችንን የሚያጠናክርበትን እድገታችንን የሚደግፍ እንዲሁም፤ ለቀጣዩ ትውልድ የሚያገለግልበትን የወደፊት ጊዜ በመንደፍ ተቋማቱን እየገነባን ነው" ሲሉም ተናግረዋል፡፡

በእውቀት እና በመከባበር ላይ የተመሰረተ ትብብር ለማድረግ ቆርጠናል" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፤ "ትብብርን፣ የቴክኖሎጂ ሽግግርን እና የደህንነት ስልጠናዎችን በደስታ እንቀበላለን እናም የኢኮኖሚያችንን እውነታ እናንጸባርቃለን" ሲሉ አስታውቀዋል፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ