መስከረም 15/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር "በትክክለኛ መንገድ ላይ ነን ለማለት አይቻልም፡፡ በውጤታማነት ላይ ያለውን ችግር በልዩ ሁኔታ ማስተካከል ያስፈልጋል" ሲል አሳስቧል።

ማኅበሩ በ2017 ዓ.ም. የትምህርት ዘመን የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ እና የዩኒቨርሲ መግቢያ ፈተናን አንድም ተማሪ ያላሳለፉ እና አነስተኛ ቁጥር ያለው ተማሪ ያሳለፉ የትምህርት ተቋማት ላይ ትኩረት መሰጠት እንደሚገባ ገልጿል፡፡

የማኅበሩ ፕሬዝዳንት ዮሐንስ በንቲ (ዶ/ር) የዘንድሮውን የተማሪዎች ውጤት አስመልክቶ "በትክክለኛ መንገድ ላይ ነን ለማለት አያስችልም" ያሉ ሲሆን፤ በያዝነው ዓመት ወደ ዩኒቨርሲቲ ለመግባት ፈተና ከወሰዱ ተማሪዎች መካከል የ91 ነጥብ 6 በመቶዎቹ ውጤት ከ50 በመቶ በታች መሆኑ እጅግ አሳሳቢ መሆኑን ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡

ፕሬዚዳንቱ የተገኘውን ውጤት "በጣም ዝቅተኛ" መሆኑን ገልጸው፤ የተማሪዎች ውጤታማ አለመሆን ዋነኛ መንስኤዎችን በተመለከተ ሲያስረዱ፣ "የተማሪዎች ዝግጁነት ማነስ፣ የትምህርት ቤቶች ግብዓትና የመሠረተ ልማት አለመሟላት እንዲሁም የፀጥታ ስጋት ባያሉባቸው አካባቢዎች በቂ ትምህርት አለማግኘት በምክንያትነት የሚነሱ ጉዳዮች ናቸው" ብለዋል።

በተጨማሪም፤ "የመንግሥት ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች በተሻለ አቅም፣ በመምህራን ግብዓት እና በምቹ የትምህርት መሠረተ-ልማት ከሚማሩት የግል ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች ጋር መወዳደር እንዲችሉ የመንግሥት ትምህርት ቤቶችን ማጠናከር ይገባል" ሲሉ ገልጸዋል።

በተከታታይ ዓመታት የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ውጤታቸው አነስተኛ እየሆነ የቀጠለውን በመንግሥት የሚተዳደሩ ተቋማት ማጠናከር የትምህርት እኩልነትን ለማምጣት ወሳኝ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡

በመሆኑም በተለይም የተማሪዎቻቸው የፈተና ውጤት ጥሩ ያልሆነላቸው ትምህርት ቤቶች ላይ ልዩ ትኩረት እንዲሰጥ፣ አማራጭ መንገዶች እንዲፈለጉ አጽንዖት ሰጥተውበታል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ