ሕዳር 1/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) አሽከርካሪዎች ግልጽ ጉድለቶች የሚባሉት ልክ እንደ ስፖኪዮ፣ ቦሎ፣ የታርጋ ቁጥር ግልጽ ያለመሆን፣ ዝናብ መጥረጊያ አለመኖር እና ሌሎችም ቴክኒካዊ ጉድለቶች ከፈጸሙ፤ የገንዘብ መቀጮ እና መንጃ ፈቃዳቸው እስከ መንጠቅ የሚደርስ ቅጣት ይጣልባቸዋል ሲል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትራፊክ ማኔጅመንት ባለሥልጣን ለአሐዱ ሬዲዮ ገልጿል።
በባለስልጣኑ የትራፊክ ቁጥጥር እና ሁነት አስተዳደር ዳይሬክተር አቶ አያሌው አቲሳ፤ በዋናነት መሰል የቁጥጥር ሥራዎች በክረምት ወቅት የሚከሰተውን ትራፊክ አደጋ ለመቆጣጠር እንዲያስችል በትኩረት እንደሚሰራ እና በሌሎች ወቅቶች ቀጣይነት እንዳለው ተናግረዋል።
እነዚህ ተግባራት ለትራፊክ አደጋ መከሰት መንስኤ እንደሆኑም ጠቁመው፤ የትራፊክ አደጋ በሀገር እና በዜጎች ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ ዘርፍ ላይ የሚያሳድረው ጫና ከባድ መሆኑን አብራርተዋል
አሽከርካሪዎች በዋናነት ከላይ የተዘረዘሩትን የቴክኒክ ጉዳዮችን ሟሟላት ግዴታ እንዳለባቸው የገለጹት አቶ አያሌው፤ እነዚህ ጥፋቶች የተገኙባቸው አሽከርካሪዎች የገንዘብ መቀጮ እንደሚጣልባቸው ነግረውናል።
ይሕም የሚሆነው ችግሩን ለመቅረፍ እንደሆነ አክለዋል። አሽከርካሪዎች ከዚህ ድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አሳስበዋል።
በተያያዘም፤ አሽከርካሪዎች ጥፋት በሚያጠፉበት ወቅት፣ በቁጥጥር ባለመያዎች መንጃ ፍቃዳቸው ሲነጠቅ እና በልዩ ሁኔታ የመኪና ሰሌዳቸው ሲፈታ ቅጣቱን እንዲከፍሉ ማስያዣ እንጂ ቅጣት እንዳልሆነ መታወቅ አለበት ብለዋል።
መሰል ሁኔታዎችን እንደ ቅጣት አድርጎ መውሰድ ትክክል ያልሆነ አመለካከት እንዳለ በመግለጽም፤ እነዚህ አመለካከቶች መስተካከል እንዳሉባቸው ጠቁመዋል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
ግልጽ ጉድለቶችን የሚፈፅሙ አሽከርካሪዎች መንጃ ፍቃድ እስከመንጠቅ የሚደርስ ቅጣት እንደሚጣልባቸው ተገለጸ
የመኪና ሰሌዳ መፍታት እና መንጃ ፍቃድ መንጠቅ መያዣ እንጂ ቅጣት አይደለም ተብሏል