ሕዳር 1/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በማረሚያ ቤቶች ውስጥ በሕግ ጥላ ሥር የሚገኙ ዜጎች ለኮሚሽኑ አጀንዳቸውን እንዲያስረክቡ ለማድረግ የሚያስችለኝን ቅድመ ዝግጅት አጠናቅቄያለሁ ብሏል።

ኮሚሽኑ የአጀንዳ የማሰባሰብ ሥራውን የሚያከናውነው አስቀድሞ ያወጣውን መስፈርት በሚያሟሉ የተመረጡ የክልል እና የፌደራል ማረሚያ ቤቶች እንደሆነም ተነግሯል።

የኮሚሽኑ ቃል-አቀባይ አቶ ጥበቡ ታደሰ፤ “በማረሚያ ቤት ውስጥ ያሉ ዜጎችን በምክክሩ ለማሳተፍ በትኩረትና በጥንቃቄ እየተሠራ ነው። በአጭር ጊዜ ውስጥም ወደ ትግበራ ይገባል" ሲሉ ለአሐዱ ሬዲዮ ተናግረዋል።

"ምክክር ኮሚሽኑ የሕግ ታራሚዎችን በምክክር ሂደቱ ማሳተፉ የራሱ ጠቀሜታ እንዳለው አውቆ ሐሳቡን እውን ለማድረግ፣ ከፌዴራል ማረሚያ ቤት እና ከፍትሕ ሚኒስቴር ከፍተኛ ኃላፊዎች ጋር ተወያይቷል፤ ሌሎች የቅድመ ዝግጅት ስራዎችንም አጠናቋል" ሲሉም ቃል-አቀባዩ አብራርተዋል።

ኮሚሽኑ በሕግ የተጣለባቸውን ፍርድ በመፈጸም ላይ የሚገኙ ታራሚዎች አጀንዳቸውን እንዲያስረክቡና የምክክር ሂደቱ አካል እንዲሆኑ ለማስቻል፤ ከፌዴራል ማረሚያ ቤቶች በተጨማሪ በሁሉም ክልሎች ከሚገኙ የማረሚያ ቤት ኃላፊዎች ጋር እየሰራ ነው ተብሏል።

ኮሚሽኑ ከታራሚዎች ጋር ለማካሄድ ያሰበውን የአጀንዳ ማሰባሰብ ሥራ "በቅርብ ጊዜ" አከናውናለሁ ከማለት በስተቀር፤ የሚካሄድበትን ትክክለኛ ጊዜ እንዲሁም የትኞቹ ማረሚያ ቤቶች ለአጀንዳ ማሰባሰቡ እንደተመረጡ አልገለጸም።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ