መስከረም 15/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) ነገ መስከረም 16 ቀን 2018 ዓ.ም በመስቀል አደባባይ በሚከበረው የመስቀል ደመራ በዓል ምክንያት የትራፊክ መጨናነቅ እንዳይፈጠር የተወሰኑ መንገዶች ለተሽከርካሪ ዝግ ስለሚሆኑ አሽከርካሪዎች አማራጭ መንገዶችን እንዲጠቀሙ የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ አሳስቧል፡፡

የ2018 ዓ.ም የመስቀል ደመራ በዓል በሠላም እንዲከበር የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይል ዝግጅቱን አጠናቆ ወደ ስራ መግባቱን ያስታወሰው ጠቅላይ መምሪያው፤ ነገ ከረፋዱ 4:00 ሠዓት ጀምሮ እስከ መርሀ ግብሩ ፍፃሜ ድረስ ለተሽከርካሪዎች ዝግ የሚደረጉ መንገዶችን ይፋ አድርጓል፡፡

በዚህም መሠረት፦
• ከቅዱስ ኡራኤል አደባባይ ወደ መስቀል አደባባይ የሚወስደው መንገድ ቅዱስ ኡራኤል አደባባይ፣

• ከቦሌ አቅጣጫ ወደ መስቀል አደባባይ ለሚመጡ ተሽከርካሪዎች ኦሎምፒያ አደባባይ ላይና ታች እንዲሁም ግራና ቀኝ፣

• ከመስቀል ፍላወር ወደ ኦሎምፒያ የሚወስደው መንገድ ጋዜቦ አደባባይ፣

• ከአጎና ሲኒማ ወደ መስቀል አደባባይ ለከባድ ተሽከርካሪ አጎና ሲኒማ አጠገብ እንዲሁም ለቀላል ተሽከርካሪ ጥላሁን አደባባይ (አራተኛ ክፍለ ጦር)፣

• ከለገሀር መብራት ወደ መስቀል አደባባይ ለገሀር መብራት፣

• ከቴሌ ማቋረጫ ወደ ስታድዮም ለሚጓዙ ቴሌ ማቋረጫ፣

• ከራስ ሆቴል ወደ ስታድየም ለሚመጡ ተሽከርካሪዎች ራስ ሆቴል፣

• ከሐራምቤ መብራት ወይም ከአምባሳደር ሲኒማ ወደ መስቀል አደባባይ ሃራምቤ መብራት፣

• ከብሔራዊ ቤተ መንግስት ወደ መስቀል አደባባይ የሚወስደው መንገድ ብሔራዊ ቤተ መንግስት አጠገብ፣

• ከዛንቺስ ሼል ወደ ባምቢስ የሚወስደው መንገድ ከዛንቺስ ሼል አጠገብ፣ እንዲሁም

• ከጁፒተር ሆቴል ወደ ECA የሚወሰደው መንገድ ባምቢስ ሳልኮት ሕንጻ አጠገብ እስከ መርሀ ግብሩ ፍፃሜ ድረስ መንገድ የሚዘጋ መሆኑን አስታውቋል፡፡

በተጨማሪም በተገለጹት መስመሮች ላይ ተሽከርካሪዎችን ለአጭርም ይሁን ለረዥም ጊዜ ማቆም የተከለከለ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፤ አሽከርካሪዎች አማራጭ መንገዶችን በመጠቀም አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርጉ የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ጥሪውን አቅርቧል።

ሕብረተሰቡ ለፀጥታ ስጋት የሆኑ አጠራጣሪ ነገሮች ሲያጋጥሙት በ011-1-11-01-11 እንዲሁም በ991 ነፃ የስልክ መስመር ጥቆማ በመስጠትና አስፈላጊውን ትብብር በማድረግ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣም ጥሪ አስተላልፏል፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ