ጥቅምት 28/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) በዴንማርክ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር የሚመራውና በግብርና፣ በአየር ንብረት ለውጥ መቋቋም፣ በሰብአዊ መብት አያያዝ እንዲሁም በመሰረተ ልማት ዝርጋታ ላይ ያተኮሩ ሥራዎችን በመስራት የሚታወቀው danida fellowshiop centre (DFC) በኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ በሰዎች ጤና እና እንቅስቃሴ ላይ የሚያሳድረውን ተፅዕኖ ለመመከት የሚያስችል ውይይት አካሂዷል።

Post image

ተቋሙ በትናንትናው ዕለት በዴንማርክ ሀገር ስልጠና የወሰዱ ባለሙያዎችንና ምሁራንን በማሰባሰብ ነው፤ "የኢትዮጵያ ዳኒዳ አልሙኒ ኔትወርክ" (ethiopian danida alumni network) የውይይት መድረክን በአዲስ አበባ ያካሄደው።

በዚህም ለዘላቂ የወደፊት የአየር ንብረት ለውጥ፣ ጤና እና የሰዎች እንቅስቃሴ በኢትዮጵያ ያለበትን ሁኔታ እና ምን መፍትሄ መወሰድ እንዳለበት የሚጠቁሙ ጉዳዮች መነሳታቸውን የኢትዮጵያ ዳኒዳ አልሙኒ ኔትወርክ አስተባባሪ አቶ ሄኖክ አጥናፌ ለአሐዱ ገልጸዋል።

በዘርፍ የተሰማሩ የምሁራንና በዴንማርክ ሀገር ሰልጥነው የመጡ ሰልጣኞች ስብስብ እ.ኤ.አ ዲሴምበር 2023 በኢትዮጵያ ዴንማርክ ኤምባሲ የድርጊት መርሀግብር በመቅረፅና የተለያዩ ስልጠናዎችን በመስጠት መመስረት መቻሉን አንስተዋል።

Post image

በዚህ ጊዜም በዛ ያሉ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ጨምሮ በተለያዩ ተቋማት ላይ ትስስር በመፍጠር የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም የሚያስችሉ እና ሌሎችም በርካታ ሥራዎች መሰራታቸውን ገልጸዋል።

በትናንትናው ዕለት የተካሄደው ውይይትም ባለፈው ዓመት የተሰሩ ሥራዎችን በመገምገም እና ከዴንማርክ የተወሰዱ ስልጠናዎችን ወደ ሥራ ለመቀየር እንዲሁም፤ በቀጣይ ዓመት ለመስራት በታቀዱ ጉዳዮች ስምምነት ላይ ለመድረስ ያለመ መሆኑን አስተባባሪው ተናግረዋል።

ለዚህ ሥራ ደግሞ የዴንማርክ ኤምባሲ የገንዘብ ድጎማን ጨምሮ የተለያዩ ድጋፎችን እያደረገ እንደሚገኝ አንስተዋል።

በዚህም መሠረት በተፈጠረው ግንኙነትና የውይይት መድረክ በቀጣይ የአየር ንብረት ለውጥ በኢትዮጵያ የሰዎች ጤና እና እንቅስቃሴ ላይ የሚያሳደረውን ተፅዕኖ መመከት የሚያስችል ጥናቶችን በማካሄድ የተለያዩ ሥራዎች እንደሚሰሩ ተገልጿል።

በተጨማሪም "በኢትዮጵያ ዳኒዳ አልሙኒ ኔትወርክ" አማካኝነት የቀድሞ ሰልጣኞችና ተማሪዎች እርስ በእርስ በመገናኘት በጋራ ጥናትና ምርምር፣ የአቅም ግንባታ እና የእውቀት ልውውጥ በማድረግ ኢትዮጵያን እና ዴንማርክን የሚጠቅሙ እድሎችን እንደሚፈጥሩ ይጠበቃል ተብሏል።

ባለፉት አስርት ዓመታት ውስጥ ከ1 ሺሕ በላይ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን በዴንማርክ ተቋማት ውስጥ በተለያዩ ደረጃዎች እና የሙያ ዘርፎች ስልጠና መውሰዳቸው ተገልጿል።

በአሁኑ ወቅትም በኢትዮጵያ እና በዴንማርክ መካከል ያለው የሁለትዮሽ ግንኙነት እየጨመረ በመምጣቱ ይህ ቁጥር በሚቀጥሉት ዓመታት በከፍተኛ ደረጃ ይጨምራል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተጠቁሟል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ