መስከረም 28/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) ጅቡቲን እና ኢትዮጵያን የሚያገናኘው መንገድ በመበላሸቱ ለአስፈላጊ የጊዜ ብክነትና ወጪ እየተጋልጥን ነው ሲሉ አሽከርካሪዎች ለአሐዱ ቅሬታ ያቀረቡ ሲሆን፤ 40 ኪሎ ሜትር የሚሆነውን መንገድ ለማለፍ እስከ 13 ሰዓት እንደሚፈጅባቸው ተናግረዋል፡፡
ከዚህ ጋር በተያያዘም መንገዱ ባለመሰራቱ ተሸከርካሪዎችን እየሰበረ እና ላልተፈለገ ወጭ እየዳረጋቸው መሆኑን ቅሬታ አቅራቢዎቹ ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡

ጉዳዩን አስመልክቶ አሐዱ ለኢትዮጵያ የከባድ ጭነት ተሸከርካሪ አሽከርካሪዎች ማህበር ጥያቄ ያቀረበ ሲሆን፤ የማህበሩ ሥራ አስኪያጅ አቶ ሰለሞን ዘውዱ ችግሩ መኖሩን እና በተለይም ተሸከርካሪዎች ጉዳት ሲደርስባቸው አሽከርካሪዎች ለአላስፈላጊ ወጭ እንደሚዳረጉ ገልጸዋል፡፡
"ከዚህ በፊት በአንድ ወር ውስጥ 2 ጊዜ ከጅቡቲ ኢትዮጵያ መመላለስ ይቻል ነበር" ያሉት የማህበሩ ሥራ አስኪያጅ፤ አሁን ግን ባለው የመንገድ ብልሽትና ሌሎችም ምክንያቶች አንድ ጊዜም ተደርሶ ላይመጣ ይችላል ሲሉ ነው የገለጹት፡፡
ብልሽት የገጠመው መንገድ ያለው የጅቡቲ ክልል ውስጥ በመሆኑ፤ የኢትዮጵያ መንግሥት በቀጥታ ሄዶ መስራት የማይችል መሆኑም ችግሩ በፍጥነት እንዳይፈታ አድርጎታል ብለዋል፡፡
መገንባት እና መስተካከል የሚችለው በጅቡቲ መንግሥት ብቻ የሆነው ይህ መንገድ፤ የከባድ ጭነት ተሸከርካሪዎች የሚመላለሱበት እና ከወደብ እቃዎችን ተረክበው ወደ ሀገር ውስጥ የሚያስገቡበት ነው ሲሉ የማህበሩ ዋና ሥራ አስኪያጅ አክለው ገልጸዋል፡፡
የተበላሸው መንገድ ርዝመት በፊት ከነበረው 80 ኪሎ ሜትር አሁን ላይ ወደ 40 ኪሎ ሜትር ያጠረ ቢሆንም፤ ይህን መንገድ ለማቋረጥ እስከ 13 ሰዓታት የሚፈጅ ከመሆኑም በላይ የተሸከርካሪን ባለስትራ ብቻ ሳይሆን ሻንሲ የሚሰብርበት አጋጣሚ ብዙ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡
"የተነሳው ችግር እንዲፈታ ለማድረግ ምን እየተሰራ ነው?" ሲል አሐዱ ለትራንስፖርት እና ሊጅስቲክስ ሚኒስቴር ጥያቄ ቢያቀርብም ምላሽ ማግኘት አልቻለም፡፡
የማህበሩ ሥራ አስኪያጅ አቶ ሰለሞን ዘውዱ ግን ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጋር በተደረገ ንግግር አሽከርካሪዎች የመኪና ብልሽት ሲገጥማቸው ጅቡቲ ላሉት የሚመለከታቸው ተወካዮች አመልክተው ከኢትዮጵያ ደብዳቤ ተፅፎ የመለዋወጫ እቃዎችን ያለቀረጥ አስገብተው ተሽከርካሪው እንዲጠገን የሚደረግበት አሰራር መኖሩን ገልጸዋል፡፡
ሆኖም ግን ይህ አይነቱ አሰራር ችግሩን በዘላቂነት የሚፈታው እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡
የመንገድ ላይ መጉላላቶች ሲያጋጥሙ ፈተና ውስጥ የሚወድቁት ከባለሃብቶቹ እና ሌሎችም አገልግሎት ፈላጊዎች በፊት አሽከርካሪዎች መሆናቸውም፤ ጉዳዩን አሳሳቢ እንዳደረገውና ዘላቂ መፍትሄን የሚሻ እንደሀሳብ አክለው ገልጸዋል፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ