የኤርትራ መንግሥት፣ የትግራይ ታጣቂዎች እና በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሱ ታጣቃዊች ከሰሞኑ ጥቃት ከፍተውበት እንደነበር የአማራ ክልል ኮሙኒኬሽን አስታውቋል፡፡

የአማራ ክልል ኮሙኒኬሽን በክልሉ ያለውን ግጭት ለመፍታት የሰላም ምክር ቤት የተቋቋመ ቢሆንም፤ ታጣቂ ሐይሎች የሀገር ሽማግሌዎችን ጭምር እያገቱ ገንዘብ እየጠየቁ ነው ሲል ገልጿል፡፡

ኢትዮጵያ የቆመችበት የሰላምና መረጋጋት ሁኔታ ከመቼውም ጊዜ በላይ እጅግ አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱን ብዙኃን ይገልጻሉ።

የፌደራል መንግሥት የክልል ልዩ ኃይል አደረጃጀቶች እንዲፈርሱ መወሰኑን ተከትሎ፤ 'የአማራ ልዩ ኃይል አይፈርስም' የሚሉ በርካታ ተቃውሞዎች መካሄዳቸው ይታወሳል፡፡

ተቃውሞውን ተከትሎ በሚያዝያ 2015 ዓ.ም. የፌደራልና የአማራ ክልል መንግሥታት በክልሉ የሕግ የማስከበር ዘመቻ መጀመራቸውን ይፋ አድርገው ነበር።

ውሳኔውን በማይቀበሉ አካላት ላይ የሕግ ማስከበር እርምጃ እንደሚወስድ የገለጸው መንግሥት መከላከያ ሠራዊትን በክልሉ የተለያዩ ቦታዎች ማሰማራቱ ከተገለጸ ወዲህ፣ ባለፈው ሚያዝያ ግጭቱ ሁለት ዓመታትን ደፍኗል።

ከሚያዝያ 2015 ዓ.ም. ጀምሮ የተቀሰቀሰው የአማራ ክልል ግጭት ከነጠቀው ሕይወት ባሻገር ነዋሪዎች መራር መከራና ተስፋ መቁረጥ ውስጥ እንዲገቡ እንዳደረጋቸው ይናገራሉ።

በተለይም ከሰሞኑ በሰሜን ወሎ ተቀስቅሶ በነበረው ግጭት "በክልሉ የትግራይ ታጣቂዎችና የኤርትራ መንግሥት ተሳትፈዋል" የሚል ወቀሳ የክልሉ ኮሙኒኬሽን መግለጹም ይታወሳል፡፡

በርካታ ዜጎች መስዋዕትነት ከፍለዋል ያሉት ኮሙኒኬሽን ኃላፊው ይህንን ድርጊት በመቃወም በርካታ የአከባቢው ነዋሪ ሰላማዊ ሰልፍ ከማድረግ በተጨማሪ ወደ መከላከያ ሠራዊት እየተቀላቀለ ነው ሲሉም ገልጸዋል፡፡

ነገር ግን የክልሉ መንግሥት ይህንን ግጭት ለማቆም በርካታ ጥረቶችን ሲያደርግ መቆየቱን የሚገልጹት የክልሉ ኮሙኒኬሽን ኃላፊ መንገሻ ፋንታው (ዶ/ር)፤ "ከሚገባን ርቀት በላይ ሄደናል" ብለዋል፡፡

በተደጋጋሚ የሰላም ጥሪ ማድረጋቸውን ገልጸው፣ "ድርድር በመጠየቃቸው ለድርድር ዝግጁ ነበርን፤ ይህንንም ግን አልተቀበሉም" ሲሉ ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡

አማራ ክልልን ለችግር የዳረገው ግጭት መቼ እንደሚያበቃ የታወቀ ጉዳይ አይደለም የሚሉ በርካቶች ናቸው፡፡

ለዚህ እንደ ምክንያት የሚያቀርቡት ደግሞ በክልሉ ግጭት ከጀመረ ወዲህ አንድም ጊዜ ግልጽ የሆነ ውይይት ወይም ድርድር አለመከናወኑ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን (ኢሰመኮ) እና ዓለም አቀፍ የመብት ድርጅቶች በተለያዩ ጊዜያት ባወጧቸው ሪፖርቶች ላይ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰላማዊ ሰዎች ተገድለዋል፣ ጉዳት ደርሶባቸዋል፤ እንዲሁም ከመኖሪያቸው ተፈናቅለዋል።

የክልሉ መንግሥትም ይህንን ስቃይና ውድመትን ለማቆም የሰላም ጥሪዎችን እያደረገ መሆኑን የገለጹት የክልሉ ኮሙኒኬሽን ኃላፊ ዶ/ር መንገሻ፣ የሰላም ካውንስሉም ጥረቶችን እያደረገ ቢሆንም በታጣቂዎች ጥቃትና እገታ ይደርስበታል ብለዋል።

ሽግሌዎች ለውይይት ቢሄዱም ታጣቀዊች ሽማግሌዎችን ጭምር እያገቱ ገንዘብ ይጠይቃሉ ሲሉ ታጣቂ ቡድኑን ክፉኛ ይኮንናሉ፡፡

ይህንን የኮሙኒኬሽኑ ሀሳብ የማይቀበሉት የእናት ፓርቲው ፖለቲከኛ ጌትነት ወርቁ አሁን ላይ የተፈጠረውን ግጭት በሽምግልና ብቻ ለመፍታት መሞከር ተገቢ አለመሆኑን በመግለፅ፤ "መንግሥትም ሆነ ታጣቂ ኃይሎች ጽናትና ስክነት ያስፈልጋቸዋል" ሲሉም ተናግረዋል፡፡

ፖለቲከኛው ጨምረውም መንግሥት "የመደራደር ፍላጎት በጽኑ ማሳየት አለበት" ሲሉ ገልጸዋል፡፡

መንግሥታት ኃይልን በብቸኝነት የመጠቀም እና የሕግ የበላይነትን የማስጠበቅ ኃላፊነት በሕግ ጭምር የተሰጣቸው የሥልጣን አካላት ናቸው፡፡

ይህንን ኃላፊነት መንግሥታት አይጠቀሙበትም ወይም ደግሞ በተሳሳተ መንገድ ከልክ ባለፈ ሁኔታ ሲጠቀሙበት ይታያል፡፡

የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ፓርቲ /ኢህአፓ/ ሊቀመንበር መጋቢ ብሉይ አብርሃም ሃይማኖት፤ "ኢትዮጵያውያን በሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ተስፋ ቆርጠናል" ያሉ ሲሆን፣ ምክንያታቸውንም ሲያስረዱ መንግሥት ለሰላም ቁርጠኛ አይደለም" ሲሉ ይከሳሉ፡፡

በአማራ ክልል እየተካሄደ ያለው ግጭት ሁለት ዓመት ቢያስቆጥርም እስካሁን ሰላም ለማምጣት የሚያስችል ፍንጭ አልታየም፡፡

በዚህም ምክንያት በክልሉ ሕዝብ እና አጠቃላይ እንቅስቃሴ ላይ ከፍተኛ ምስቅልቅል መፍጠሩ ይገለጻል።

ክልሉን ቀውስ ውስጥ ያስገባውን ግጭት ለማስቆም የአማራ ክልል እና የፌደራሉ መንግሥት ለድርድር በራቸው ክፍት መሆኑን ቢገልጹም እንዲሁም ሁለቱን ወገኖች የሚያሸማግል ምክር ቤት ቢቋቋምም፤ እስካሁን በተጨባጭ የተገኘ ውጤት ስለመኖሩ በይፋ የተባለ ነገር የለም።

ነገር ግን በርካታ ፖለቲከኞች መንግሥት "ሐቀኛ ድርድር የማድረግ ፍላጎቱን ማሳየት አለበት" ይላሉ።

ይህንን በሚመለከት በያዝነው ሳምንት መጀመሪያ ሰኞ 6ኛው የኢፌዲሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና የፌዴሬሽን ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን መክፈቻ ሥነ ሥርዓት ተካሂዷል፡፡

በዚህ ወቅት የመንግሥትን ዓመታዊ አቅጣጫ አስመልክቶ ንግግር ያደረጉት ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ፣ ግጭቶችን መንግሥት በኃይል ለመፍታት አቅም ያለው ቢሆንም ቂም እና ቁርሾን ላለማውረስ በውይይትና በእርቅ እንዲፈታ እያደረገ መሆኑን በምክር ቤቶቹ የመክፈቻ ሥነ ሥርዓት ላይ ተናግረዋል፡፡

በአማራ ክልል ያለው ግጭት ከፈጠረው አጠቃላይ ቀውስ አንጻር የሰላም መፍትሄ ቢገኝ ብዙዎች የሚጠይቁት ነው።

እስከአሁን ግን ያንን የሰላም አማራጭ የሚያሳዩ ሁኔታዎች እየተፈጠሩ ካለመሆናቸው በተጨማሪ፣ ግጭቱ ከዚህም በላይ እንዳይባባስ በነዋሪው ላይ ስጋትን ፈጥሯል፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ