ሰኔ 23/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) 30 በመቶ ቅድመ ክፍያ ከፍለን በ6 ወራት ውስጥ ተሸከርካሪ ሊያቀርብልን ከኤል አውቶ ኢንጂነሪንግ እና ትሪዲንግ ኃ/የተ/የግል ኩባንያ ጋር ብንዋዋልም፤ ተፈጻሚ ሳይሆን አምስት ዓመት ሆኗል ሲል የአራራይ የታክሲ ዘርፍ ማህበር አባላት ቅሬታቸውን ለአሐዱ አቅርበዋል።

ቅሬታ አቅራቢዎቹ በስድስት ወራት ውስጥ የተሸከርካሪ ባለቤት ለመሆን በኤል አውቶ ኢንጂነሪንግ እና ትሪዲንግ ኃ/የተ/የግል ኩባንያ የተጠየቁትን 30 በመቶ ቅድመ ክፍያ ቢከፍሉም፤ ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ እስከአሁን ድረስ ተፈጻሚ እንዳልሆነላቸው ተናግረዋል።

ከ550 በላይ የሚሆኑ አባላትን የያዘው የአራራይ የታክሲ ዘርፍ ማህበር አባላት፤ የከፈሉትን ገንዘብ እንዲመለስላቸው በተደጋጋሚ በጹሁፍና በአካል ቢጠይቁም ምላሽ እየተሰጣቸው እንዳልሆነ አብራርተዋል።

በተጨማሪም በወቅቱ በ2012 እና በ2013ዓ.ም የነዳጅ ተሸከርካሪዎች እንዲቀርቡላቸው የተዋዋሉ ሲሆን፤ የተወሰነ የዋጋ ጭማሪ በማድረግ የኤሌክትሪክ ተሸከርካሪዎች እንዲመጡላቸው መስማማታቸውን አብራርተዋል።

በዚህም የኤሌክትሪክ ተሸከርካሪዎችን ለማምጣት በቂ የገንዘብ ብድር እንዲሰጥ በሚል ከሦስተኛ ወገን ጋር ማለትም ከታክሲዬ የገንዘብ ቁጠባና ብድር ህብረት ሥራ ማህበር ጋር እንዲዋዋሉ መደረጉን ተናግረዋል።

Post image

በአጠቃላይ በአሁኑ ወቅት የተወሰኑ የኤሌክትሪክ ተሸከርካሪዎች እንደመጡ ገልጸው፤ ነገር ግን የመጡት ተሸከርካሪዎች ከውሉ ውጭ የሆኑና ከተዋዋሉት ገንዘብ በእጥፍ ጨምረው እንዲከፍሉና እንዲወስዱ እየተጠየቁ መሆኑን ለአሐዱ ገልጸዋል።

አሐዱም ይህንን ቅሬታ በተመለከተ ከኤል አውቶ ኢንጂነሪንግ እና ትሪዲንግ ኃ/የተ/የግል ኩባንያ የኮሙንኬሽንና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዳይሬክተር አቶ ኢሳያስ ታፈሰን አነጋግሯል።

በምላሻቸውም በውሉ መሠረት ላለመፈጸሙ የተለያዩ ምክንያቶች መኖራቸውን አንስተው፤ በዋናነት የኮቪድ መከሰት፣ አምራች ድርጅቶች የሞዴል ለውጥ ማድረጋቸው እንዲሁም አበዳሪ ድርጅት መታጣቱ መሆኑን አብራርተዋል።

በዚህም ለእያንዳንዱ ክስተት ከማህበሩ አባላት ጋር ውይይት መደረጉን የገለጹት አቶ ኢሳያስ፤ "የዋጋ ጭማሪንም በተመለከተ የዶላር ጭማሪ በመኖሩ የተደረገ ነው" ብለዋል።

በተጨማሪም የገቡ የኤሌክትሪክ ተሸከርካሪዎችን በተመለከተ፤ ከማህበሩ ግማሽ በመቶ የሚሆኑት ተስማምተው እየወሰዱ መሆኑን ገልጸዋል።

እንዲሁም 'ገንዘብ ይመለስልኝ' የሚል አካልም እየተመለሰለት መሆኑንና አሁንም እንዲመለስላቸው የሚፈልጉ ካሉ መጠየቅ እንደሚችሉ ተናግረዋል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ