ሰኔ 23/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በኢትዮጵያ ያለው ዓመታዊ የዋጋ ግሽበት እየቀነሰ መጥቶ በሚያዝያና በግንቦት ወር 2017 መጨረሻ 14 ነጥብ 4 በመቶ መድረሱን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የገንዘብ ፖሊሲ ኮሚቴ አስታወቀ፡፡
ምግብ-ነክ የዋጋ ግሽበት ግንቦት ወር 2017 መጨረሻ 12 ነጥብ 1 በመቶ፣ ባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከነበረው 25 ነጥብ 6 በመቶ ጋር ሲነጻጸር ቅናሽ ማሳየቱም ገልጿል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የገንዘብ ፖሊሲ ኮሚቴ በዛሬው ዕለት ባከናወነው ሦስተኛ ስብሰባው፤ የኢትዮጵያን የዋጋ ግሽበት፣ የፊስካል፣ የውጭ ኢኮኖሚ፣ የገንዘብ አቅርቦትና የፋይናነስ ዘርፍ አዝማሚያዎችን፣ አጠቃላይ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ አመልካቾችን እንዲሁም በሀገር ውስጥ የማክሮ ኢኮኖሚ ሁኔታዎች ላይ ጉልህ አንደምታ ያላቸው ዓለም አቀፍ ሁኔታዎችን ገምግሟል።
በዚህም የብሔራዊ ባንክ የፖሊሲ ተመን አሁን ባለበት 15 በመቶ እንዲቆይና የዋጋ ግሽበት የመርገብ አዝማሚያ ማስቀጠል አስፈላጊ በመሆኑ፤ 18 በመቶ ዓመታዊ የብድር ዕድገት ጣሪያ እስከ ቀጣዩ የመስከረም ወር 2018 የገንዘብ ፖሊሲ ኮሚቴ ስብሰባ ጊዜ ድረስ ባለበት እንዲቆይ ውሳኔ አሳልፏል፡፡
በዚህም በውጪ ኢኮኖሚ ዘርፍ ባደረገው ግምገማ በዓለም አቀፍ የዋጋ ግሽበት በአንዳንድ ሀገራት የማንሰራራት አዝማሚያ እንደሚያሳይ ቢገመትም፤ በጥቅሉ ግን የመቀነስ አዝማሚያ እንደሚኖር ይጠበቃል ሲል በመግለጫው ገልጿል።
የዋጋ ግሽበቱ ምንም እንኳን እ.ኤ.አ በጥር ወር 2025 ከተተነበየው ያነሰ ቢሆንም እ.ኤ.አ በ2025 መጨረሻ ወደ 4 ነጥብ 3 በመቶ ዝቅ እንደሚል ግምቱን ቢያስቀምጥም፤ "አሁን ላይ እየተስተዋሉያሉ የጂኦ- ፖለቲካ አዝማሚያዎች እና የዓለም አቀፍ የታሪፍ ማሻሻያዎች በዓለም አቀፍ የዋጋ ግሽበት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ሊያደርሱ እንደሚችሉ ስጋት አለ" ብሏል።
በአንጻሩ በተመሳሳይ ወቅት 17 ነጥብ 8 በመቶ የደረሰው ምግብ-ነክ ያልሆነ የዋጋ ግሽበት ከአምናው ጋር ሲነጻጸር ቅናሽ ያሳየ ቢሆንም፤ ከቅርብ ወራት ወዲህ በተወሰነ መልኩ እያንሰራራ ይገኛል ተብሏል፡፡
ላለፉት በርካታ ዓመታት ሲንከባለል የመጣው የዋጋ ግሽበት አሁን ካለበት ደረጃ በይበልጥ መውረድና የኑሮ ውድነትም በሕብረተሰቡ ላይ እያሳደረ ያለው ከባድ ጫና ለማቅለል፣ ይህንንም ግብ ለማሳካት ብሔራዊ ባንክ ጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲ መተግበሩን መቀጠል እንደሚገባው ኮሚቴው አሳስቧል።
እንዲሁም በመግለጫው የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ፣ የገንዘብ ሁኔታ፣ የወለድ ተመን እና የፊሲቻል ሁኔታ በተመለከተ የታዩ ሥራዎችን በዝርዝር ገልጿል።
በተጨማሪም "ንግድ ባንኮች የረጅም ጊዜ የግምጃ ቤት ቦንድ እንዲገዙ የሚያስገድደው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መመሪያ እንዲነሣ እንዲሁም፤ ብሔራዊ ባንክ እንደ አስፈላጊነቱ ገበያ- መር የሆነ የገንዘብ ፖሊሲ መሣሪያዎችን ይጠቀማል" ሲል ገልጿል።
ኮሚቴው ቀጣዩን ስብሰባውን በመስከረም ወር 2018 መጨረሻ ወይም እንደ አስፈላጊነቱ ከዚያ ቀደም ብሎ እንዲከናወን መወሰኑም ተነግሯል፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
በኢትዮጵያ ያለው ዓመታዊ የዋጋ ግሽበት እየቀነሰ መምጣቱን ብሔራዊ ባንክ ገለጸ
የባንኮች 18 በመቶ ዓመታዊ የብድር ዕድገት ጣሪያ እስከ ቀጣዩ የመስከረም ወር ድረስ ባለበት እንዲቆይ ውሳኔ ተላልፏል
