ሰኔ 23/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በቅርቡ ለተከሰተው ኤምፖክስ ወይም የዝንጀሮ ፈንጣጣ ወረርሽኝ አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት በሁለት ሚሊዮን ቤቶች ላይ የቅኝት ሥራ መሰራቱን የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ለአሐዱ አስታውቋል፡፡

በሀገር-አቀፍ ደረጃ በተከሰተው የዝንጀሮ ፈንጣጣ ወረርሽኝ የተጠቃ አንድ ሰው፤ በኦሮሚያ ክልል ሞያሌ ከተማ ለመጀመሪያ ጊዜ መገኘቱን ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ግንቦት 16 ቀን 2017 ዓ.ም. ማስታወቁ የሚታወስ ሲሆን፤ በወረርሽኙ ምክንያት እስካሁን ድረስ የአንድ ሰው ሕይወት ማለፉ ይታወቃል።

አሐዱም "ወረርሽኙን ለመቆጣጠር ምን እየተሰራ ነው?" ሲል የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩትን ጠይቋል።

የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መሳይ ሃይሉ በሰጡት ምላሽ፤ "ለወረርሽኙ አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት በተደረገው ጥረት በ2 ሚሊዮን ቤቶች ላይ የቅኝት ሥራ ተሰርቷል" ብለዋል፡፡

እስካሁን በተደረገው ምርመራም በ24 ሰዎች ላይ በሽታው መገኘቱን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ከነዚህም ውስጥ 20ዎቹ በተደረገላቸው የሕክምና ክትትል አገግመው ወደ ማህበረሰቡ መቀላቀላቸውን ተናግረዋል። ሌሎች አራት ሰዎች ደግሞ ሕክምና በመከታተል ላይ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

Post image

በተጨማሪም "ወረርሽኙን ለመቆጣጠር ብሔራዊ የማገገሚያ ማዕከል ተዘጋጅቷል፤ ሕመምተኞች በተሻለ መንገድ እንዲያገግሙ እየተደረገ ነው" ሲሉም ዳይሬክተሩ ለአሐዱ ገልጸዋል።

"ሆኖም በጤናው ዘረፍ በቂ የሆነ ሥራ ስርተናል ማለት የምንችለው ወረርሽኞችን ስጋት ወደ ማይሆኑበት ደረጃ ማድረስ ስንችል ነው" ብለዋል።

"ከዚህ አንጻር ጥሩ ጅምር አለ" የሚሉት ዶ/ር መሳይ፤ ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ችግሮች በጤናው ዘርፍ ላይ አሉታዊ ጫና እያሳደሩ ነው ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል፡፡

በዚህም ዳይሬክተሩ "ሁሉም የሰላም በሮች ተከፍተው የጤና ተቋማት በሚፈለገው መልክ ለማህበረሰቡ አገልግሎት የሚሰጡበትን ዕድል መፍጠር ያስፈልጋል" ሲሉ አሳስበዋል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ