መስከረም 14/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) ለአዳዲስ ተማሪዎች ከማህበረሰቡ ቤተሰብ በመመደብ ተማሪዎች የእንግዳ ስሜት ሳይሰማቸውና ተቀራርበው እንዲኖሩ ለማስቻል ያለመውን የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የቃል ኪዳን ቤተሰብ ፕሮጀክትን በተመለከተ የሰላም ሚኒስቴር ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎችም ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባቸው አቅጣጫ ማስቀመጡን ተከትሎ፤ አሐዱ ያነጋገራቸው የጅማ እና የመቀሌ ዩኒቨርሲቲዎች ፕሮጀክቱን ለማስጀመር ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የጅማ ዩኒቨርሲቲ የውጪ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ሴኔት ዳይሬክተር ፍሬው አምሳሉ፤ ከዚህ ቀደም በነበረው የአሰራር ልማድ መሠረት አዳዲስ ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርሲቲው ሲሄዱ አባገዳዎች፣ ሀደ ሲንቄዎች፣ የሐይማኖት አባቶች እና የከተማው ወጣቶች ከነባር ተማሪዎች ጋር በመሆን አቀባበል እንደሚደረግላቸው አንስተዋል።

ከገቡ በኋላም በተለያየ መንገድ ተማሪዎች ከማህበረሰቡ ጋር ተቀራርበው እንዲኖሩ የሚያደርግ ሥራዎች ይሰራሉ ብለዋል።

ከዚህ በተጨማሪ ግን በዚህ ዓመት በተለየ መልኩ ማህበረሰቡ የሚሰጠውን አገልግሎት ተቋማዊ ለማድረግ፤ የሰላም ሚኒስቴር በተለይም የጎንደር ዩኒቨርሲቲን ተሞክሮ በሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች ላይ ተግባራዊ ለማድረግ ባስተላለፈው ጥሪ መሠረት የጅማ ዩኒቨርሲቲም ጎንደር ላይ በመገኘት የልምድ ልውውጥ ማድረጉን ገልጸዋል።

በዚህም መሠረት የቃል ኪዳን ቤተሰቡን በዩኒቨርሲቲው ነባራዊ ሁኔታ ሊሆን በሚችል መልኩ በማዘጋጀት፤ ከከተማው አስተዳደር፣ ከምሁራንና ከአካባቢው ታዋቂ ሰዎች የተውጣጣ አብይ ኮሚቴ መቋቋሙን አስታውቀዋል።

አቢይ ኮሚቴውም እቅድ አውጥቶ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ ገልጸው፤ በዘንድሮው ዓመት ከ200 በላይ ቤተሰቦች ለተማሪዎች ቤተሰብ በመሆን ሥራው እንዲጀመር ለማድረግ እየተሰራበት እንደሚገኝ ገልጸዋል።

አሐዱ ያነጋገራቸው የመቀሌ ዩኒቨርስቲ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ተካቦ ገብረስላሴ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ዩኒቨርስቲው ይህን መሰል ጥሪ ከመቅረቡ አስቀድሞ በነበረው አሰራር መሠረት የሚመጡ አዳዲስ ተማሪዎችን ከማህበረሰቡ ጋር ቤተሰባዊ ስሜት እንዲሰማቸው ለማድረግ በርካታ ሥራዎች እንደሚሰራ ገልጸዋል።

ወደ ዩኒቨርሲቲው በሚሄዱበት ወቅትም የመንግሥት አካላት፣ የሐይማኖት አባቶችና ማህበረሰቡ ተሰብስቦ እንደሚቀበላቸው ተናግረዋል።

በዚህም መሠረት በዘንድሮው ዓመትም በተለመደው የእንግዳ ተቀባይነት ስሜት ተማሪዎችን እንደሚያስተናግድ ገልጸው፤ ነባር ተማሪዎችን እየተቀበለ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

አዳዲስ ተማሪዎችንም እንዲሁ የትምህርት ሚኒስቴር ባስቀመጠው መርሀግብር መሰረት የቅበላ ሥነ ስርዓቱን እንደሚያካሂድ ተናግረዋል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ