መስከረም 14/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ዞን ጠለምት ወረዳ አብነት ቀበሌ ከሁለት ዓመት በፊት ከ780 በላይ አባዎራዎችና እማወራዎች በመሬት መሸራተት አደጋ መፈናቀላቸው የሚታወስ ሲሆን፤ እነዚህ ዜጎች ላለፉት 6 ወራት ምንም አይነት ድጋፍ እንዳልቀረበላቸው ተገልጿል።

150 አባወራዎችና እማወራዎች በአጠቃላይ ከእነ ቤተሰቦቻቸው 780 የሚሆኑ ዜጎች የምግብ፣ መድኃኒትና አልባሳት ድጋፍ ከቀረበላቸው ስድስተኛ ወሩን መያዙን የጠለምት ወረዳ አደጋ መከላከልና ቅድመ ማስጠንቀያ ቡድን መሪ የሆኑት አቶ መሰረት ጥላሁን ለአሐዱ ተናግረዋል።

በአንድ መጠለያ ጣቢያ ውስጥ ከ10 እስከ 15 ተፈናቃዮች እንደሚኖሩ የገለጹት የቡድን አስተባባሪው፤ በዚህም ምክንያት ለተለያዩ ተላላፊ በሽታዎች ተጋላጭም እየሆኑ ነው ብለዋል።

አደጋዉ ሲከሰት በርካታ ኢትዮጵያዊንና ሌሎች አጋር ድርጅቶች የተለያዩ ምግብ ነክና ምግብ ነክ ያልሆኑ ድጋፎችን ሲያደርጉ እንደነበር ያስታወሱም ሲሆን፤ አሁን ግን ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ አቋርጠዋል ሲሉ ለአሐዱ አስታዉቀዋል።

"የክልሉ መንግሥት ለወረዳው የሥራ ማስኬጃ በየዓመቱ በጀት እየለቀቀ ነው" የሚሉት አቶ መሰረት፤ ነገር ግን የተከሰተውን አደጋ ምክንያት በማድረግ እዚህ ግባ የሚባል ድጋፍ ወደ ወረዳው እስካሁን አላከም ሲሉ ገልጸዋል።

በሌላ በኩል ከዚህ ቀደም አደጋው የተከሰተበትን አካባቢ የጎንደር ዩኒቨርስቲ ጥናት አድርጎበት ተፈናቃዮች ወደ ቀደሞ መኖሪያ ቀዬአቸው የሚመለሱበት ምንም አይነት እድል እንደሌለ አረጋግጧል ሲሉ የቡድን መሪው ተናግረዋል።

አሐዱም ለተጨማሪ መረጃ የአማራ ክልል የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ቢሮን ለማነጋገር ጥረት ያደረገ ቢሆንም ሳይሳካ ቀርቷል።

የጠለምት ወረዳ ባጋጠመው የመሬት መንሸራተት ምክንያት 10 ሰዎች ሕይወታቸውን ሲያልፍ፣ 8 ሰዎች ከባድ ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን፤ በርካታ የቤት እንስሳቶችም በአደጋው መሞታቸው ይታወሳል።

የመሬት መንሸራተቱ ከ30 ሄክታር በላይ በሰብል የተሸፈነ መሬት ላይ ጉዳት ከማድረሱ በተጨማሪም፤ 48 ያክል ቤቶች ጉዳት እንደደረሰባቸው ተገልጿል፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ