መስከረም 15/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) በተለይም በአዲስ አበባ 5 መግቢያዎች ላይ በሚገኙ የተሽከርካሪ የቴክኒክ ምርመራ ሰጪ ተቋማት ላይ በተደረገ ድንገተኛ ፍተሻ፤ 29 ተቋማት ላይ ከባድ የአሰራር ክፍተቶች እና ሕገ-ወጥ ተግባራት መገኘታቸውን የትራንስፓርትና ሎጀስቲክስ ሚኒስቴር አስታውቋል።

በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የትራንስፖርት አገልግሎትና ቁጥጥር ዘርፍ አማካሪ አቶ አሰፋ ሀዲስ፤ በተቋማቱ ላይ የተደረገው ይህ ድንገተኛ ፍተሻ እና ምርመራ የተሸከርካሪዎች ፍተሻ ሂደት በቂ የቴክኖሎጂ ድጋፍ እንደሌለውና በሰዎች ውሳኔ ላይ ብቻ የተመሠረተ እንደሆነ ያሳየ ነው ሲሉ ለአሐዱ ተናግረዋል።

ይህም የአሰራር ጉድለት ብቃት የሌላቸው ተሽከርካሪዎች በቀላሉ ሰርተፊኬት እንዲያገኙ ምክንያት መሆኑን ገልጸዋል።

አክለውም፤ በዋናነት ተሽከርካሪዎች መብራት፣ የፍጥነት መቆጣጠሪያ እና ሌሎች ወሳኝ የደህንነት ክፍሎችን ሳያሟሉ ፍተሻውን እንደሚያልፉ የገለጹ ሲሆን፤ ይህም በከፍተኛ ደረጃ ለትራፊክ አደጋ መንስኤ እንደሆነ ገልጸዋል።

የትራንስፖርት አገልግሎት ዘርፍ ቁጥጥር አማካሪው አቶ አሰፋ፤ ችግሩን ለመፍታት እና የሰው ጣልቃ ገብነትን ለመቀነስ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በቴክኖሎጂ የተደገፈ አዲስ ስርዓት እየዘረጋ ስለመሆኑም ለአሐዱ አስረድተዋል።

ይህ ስርዓት እያንዳንዱ የተሽከርካሪ ምርመራ ውጤት በቀጥታ ከሚኒስቴሩ የመረጃ ቋት (ዳታቤዝ) ጋር የተገናኘ እንዲሆንና በሰው በኩል ምንም አይነት ማሻሻያ ማድረግ እንዳይቻል የሚያስችል ነው ብለዋል።

አዲሱ ቴክኖሎጂ ተሽከርካሪው መቼ፣ የት እና በማን እንደተመረመረ እንዲሁም ምን ያህል ውጤት እንዳመጣ ማወቅ የሚያስችል በመሆኑ፤ ከዚህ ቀደም የነበሩ ሕገ-ወጥ አሰራሮችን እንደሚያስቀርም ታምኖበታል።

በተሽከርካሪ የቴክኒክ ምርመራ ሰጪ ተቋማት ላይ የተደረገው ፍተሻ ከፌደራል ፖሊስ፣ ከአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ፣ ከትራፊክ ማኔጅመንት እና ሌሎች የጸጥታና የመንገድ ደህንነት ተቋማት ጋር በመተባበር የተከናወነ ሲሆን፤ በዚህም ብቃት የሌላቸውና ለሕዝብ አደጋ የሚያደርሱ ተሽከርካሪዎች በቀላሉ የምርመራ ሰርተፊኬት እያገኙ ወደ ሥራ እየገቡ መሆኑን በፍተሻው መረጋገጡ ተነግሯል።

አሐዱ ያነጋገራቸው በተሽከርካሪ ምርመራ ላይ የተሰማሩ ተቋማት በበኩላቸው፤ ተሽከርካሪዎች ምርመራ ካለፉና ማረጋገጫ ከተሰጣቸው በኋላ ፍተሻ ያለፉባቸውን የመኪና አካላት እንደሚቀይሩና ይህም ለችግሩ አንድ ምክንያት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በዚህ ሐሳብ የማይስማሙት አቶ አሰፋ "ሕብረተሰቡን ከሞት የማዳን ጉዳይ የሁሉም ግዴታ ነው። በሲስተሙ ውጤቱ ከታወቀ በኋላ ሰዎች ጣልቃ ገብተው ማሳለፍ ከቻሉ፣ ይህ የሰው ተጽዕኖ መኖሩን የሚያረጋግጥ ነው።" ብለዋል።

ሕይወት እና ንብረትን በማጥፋት ላይ የሚገኘውን የትራፊክ አደጋ ለመቀነስ የተሽከርካሪዎችን ደህንነት መጠበቅ አንዱ ተግባር መሆኑን አማካሪው የገለጹ ሲሆን፤ አዲሱ ቴክኖሎጂ በቅርቡ ወደ ሥራ እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ