ሰኔ 27/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ሦስተኛው የአፍሪካ የሥራ ዕድል ፈጠራ ፎረም ከሰኔ 30 እስከ ሐምሌ 2 ድረስ በአዲስ አበባ ከተማ አድዋ መታሰቢያ ሊካሔድ መሆኑን የሥራና ክህሎት ሚኒስትር አስታውቋል፡፡
የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል በዛሬው ዕለት ለጋዜጠኞች በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤ በቀጣይ የሚካሄደው ሦስተኛው አህጉር አቀፍ የሥራ ዕድል ፈጠራ ፎረም በአፍሪካ ደረጃ ያለውን ሥራ አጥነት የሚቀንስ እና ለምጣኔ ሃብታዊ እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያለው መድረክ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ፎረሙ ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን፣ ከአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጠና ሴክሬታሪያት እና የአፍሪካ ኤሌክትሮኒክ ትሬድ ግሩፕ (African Electronic Trade Group) ከተሰኘ ተቋም ጋር በመተባበር የተዘጋጀ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በዚህም አፍሪካ ያላትን እምቅ ሀብት ወደ ተጨባጭ አቅም ለመቀየር እና ሥራ አጥነትን ትርጉም ባለው መልኩ ለመቀነስ፣ ምጣኔ ሃብታዊ ያዊ ተጠቃሚነትን እና አህጉራዊ ትስስርን ለማሳደግ አላማው አድርጎ እየሰራ ነው ብለዋል፡፡
ከዚህ በተጫመሪም መድረኩ የግብርና እሴት ሰንሰለት፣ ዲጂታላይዜሽን እና የፋይናንስ አካታችነትን ለማረጋገጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ጠቅሰዋል፡፡ በተለይም ለሴቶችና ወጣቶች ምቹና አስተማማኝ የሥራ ዕድል ለመፍጠር ብሎም የአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጠና ትስስርን ወደላቀ ደረጃ ላይ በማትኮር እንደሚካሄድ ገልጸዋል፡፡
በጉባኤው ላይ ኢንቨስተሮች፣ ተመራማሪዎች፣ ሚኒስትሮች፣ ኢንተርፕራይዞችና ሌሎች የዘርፉ ተዋናዮች የሚገኙ ሲሆን፤ ኢትዮጵያ እንግዶችን ለማስተናገድ ዝግጅቷን ማጠናቀቋንም ተናግረዋል፡፡
የሥራ ፈጠራ ከውይይት ባለፈ ወደ ተግባር ወርዶ የሚሰራበትን ሁኔታ የሚፈጥር መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሯ፤ ፎረሙ በቀጣይ 15 ዓመታት ውስጥ በአፍሪካ በትንሹ ከ120 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር በእቀድ እንደሚሰራ አብራርተዋል፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
ሦስተኛው የአፍሪካ የሥራ ዕድል ፈጠራ ፎረም በአዲስ አበባ ሊካሄድ ነው
