ሕዳር 23/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) ህዝባዊ ወያነ ሀርነት ትግራይ (ህወሓት) "7ኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ በትግራይ ክልል እንዲካሄድ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የፓርቲውን ሕጋዊ ሰውነት ዳግም መመለስ አለበት" የሚል ቅድመ ሁኔታን በፓርቲው ቃል አቀባይ አቶ ሚካሄል አስገዶም በኩል ማቅረቡን ተከትሎ፤ በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተቃውሟቸውን አሰምተዋል።

አሐዱ ያነጋገራቸው ሣልሳይ ወያነ ትግራይ እና የትግራይ ነጻነት ፓርቲዎች፤ የሕወሓት እርምጃ የትግራይን ሕዝብ ለተጨማሪ የፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ቀውስ ሊዳርግ እንደሚችል ያላቸውን ስጋት ገልጸዋል።

የሣልሳይ ወያኔ ትግራይ ፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ብርሃነ አጽብሀ፤ ሕወሓት ያስቀመጠው ቅድመ ሁኔታ ሕዝቡን ለዳግም ችግር የመዳረግ እድል ስላለው "አስቸኳይ መፍትሔ ሊሰጠው ይገባል" ብለዋል።

"የችግሩ የመጨረሻ ገፈት ቀማሽ ሕዝቡ ነው" ያሉት አቶ ብርሃነ፤ ሕወሓት ሕጋዊ ሰውነቱን ማስመለስ የሚችለው ኃይልን በመጠቀም ሳይሆን በሕግና የፕሪቶሪያው ስምምነት ላይ በመመስረት ብቻ እንደሆነ አስረድተዋል።

በተጨማሪም፣ ሕወሓት 'ሕወሓት ችግር ውስጥ ነው ማለት የትግራይ ሕዝብም ችግር ውስጥ ነው' የሚል ይዘት ያለው መግለጫ ማውጣቱ፤ "ካለፈው ጦርነት ትምህርት አለመውሰዱን ያሳያል" ሲሉ ተችተዋል።

የትግራይ ነፃነት ፓርቲ ሊቀመንበር ደጀን መዝገበ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ምርጫ ከመደረጉ በፊት ከመከላከያ ሠራዊት ውጭ ያሉ የታጠቁ የሌሎች ኃይሎች ክልሉን ለቀው መውጣት እንዳለባቸውና መሰል ቅድመ ዝግጅቶች መደረግ እንደሚገባቸው ፓርቲያቸው ሐሳብ ማንሳቱን አስታውሰዋል።

ሊቀመንበሩ "ምርጫ ቦርድ 'ችግሮችን ታሳቢ ያደረገ ጥናት የተመሠረተበት ቅድመ ዝግጅት አድርጊያለሁ' ቢልም የሚታየው ነባራዊ ሁኔታ ግን የተነገረውን ዓይነት አይደለም" ያሉ ሲሆን፤ "ህወሓት ሀገራዊ ምርጫን ከራሱ ህልውና ጋር አያይዞ መቃወሙ ከፓርቲው ባህሪ አንጻር የሚጠበቅ ነው" ብለዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሕወሓትን በ2013 ዓ.ም. 'ኃይልን መሠረት ባደረገ የአመጽ ተግባር ላይ ተሳትፏል' በሚል ከፖለቲካ ፓርቲዎች መዝገብ ላይ እንደሰረዘው የሚታወስ ነው። ከዚያ በኋላ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአሸባሪነት ተፈርጆ ቢቆይም፤ ከፕሪቶሪያው ስምምነት በኋላ አሸባሪነቱ ተነስቶለት "በልዩ ሁኔታ" በፓርቲዎች ዝርዝር ውስጥ ገብቷል።

በመጨረሻም፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ 'ሕወሓት ሕጋዊ ፓርቲ ሆኖ እንዲቀጥል ማሟላት ያለበትን መስፈርት በተሰጠው የጊዜ ገደብ አላሟላም' በሚል ከግንቦት 5 ቀን 2017 ዓ.ም. ጀምሮ ከፖለቲካ ፓርቲነት ሰርዞታል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ