ሕዳር 16/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ፓርቲ፣ የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ፓርቲ፣ የአማራ ግዮናዊ ንቅናቄ፣ አንድ ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ እና እናት ፓርቲ መስከረም 10 ቀን 2018 ዓ.ም "ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት" የሚል ጥምረት መመስረታቸውን መገለጻቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለጥምረቱ ከቀናት በፊት እውቅና ሲሰጥ እናት ፓርቲን ከቅንጅቱ ማገዱን የገለጸ ሲሆን፤ 'የላዕላይ ምክር ቤት አባላት ቅሬታ ማቅረባቸው ብሎም የእናት ፓርቲ መተዳደሪያ ደንብ የላዕላይ ምክር ቤት አባላት ቁጥር 36 ሲሆን በቅንጅቱ ውሳኔ የተሳተፉ የላዕላይ ምክር ቤት አባላት 17 ብቻ መሆናቸውን' ገልጿል።

ስለሆነም እናት ፓርቲ "ስለቅንጅቱ በላዕላይ ምክር ቤቱ አስወስኖ ሲያቀርብ የቅንጅቱ አባል መሆን ይችላል" ሲል ቦርዱ ገልጿል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሰጠውን ውሳኔ በተመለከተ አሐዱ የፓርቲውን የአደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ አሰፋ አዳነ (ዶ/ር)ን ጠይቋል።

በምላሻቸውም ከዓመት በፊት የተጀመረ አካሄድ መሆኑን ጠቁመው፤ የፓርቲው የላዕላይ ምክር ቤት አባላት ቁጥር በተለያየ ምክንያት 24 መድረሱን መጋቢት 2017 ዓ.ም ማሳወቃቸውን አንስተዋል።

እንዲሁም አሁን ቅሬታ ያቀረቡትና የላዕላይ ምክር ቤት አባላት የተባሉት ሁሉም የምክር ቤቱ አባል አለመሆናቸውና ስብሰባ እንዲጠሩ ምርጫ ቦርድ ቀነ ገደብ ያስቀመጠ ቢሆንም ስብሰባውን ሳያደርጉ ቀርተዋል ብለዋል።

ቦርዱ በቀደሙት ጊዜያቶች ከፓርቲው የደረሱት ማስረጃዎች ተቀብሎ በጥምረቱ ምስረታ ላይ እስኪገኝና ፍቃድ እስኪሰጥ ድረስ ምንም አይነት እርማት እንዲደረግ አለመጠየቁን ዶ/ር አሰፋ ገልጸዋል።

በቅንጅቱ ምስረታ ዝግጅት ወቅት ፓርቲዎቹ ያሳለፉትን ውሳኔ ቃለ ጉባኤ እና የሚመሠረተው ቅንጅት ረቂቅ መተዳደሪያ ደንብ ለምርጫ ቦርድ ተልኮ ቦርዱም ሰነዶቹን ከመረመረ በኋላ በመተዳደሪያ ደንቡ ላይ ብቻ መጠነኛ ማስተካከያዎች እንዲደረጉ በማሳሰብ የቀረቡለትን ሰነዶች መርምሮ በቅንጅቱ መስራች ጉባኤ ተገኝተው የሚታዘቡ ሠራተኞቹ በታደሙበት ጉባዔ በዕለቱ የቅንጅቱ ምስረታ መፈጸሙን አስታውሰዋል።

"ቦርዱ መሰረታዊ የሆነ ምክንያት እንዲሰጠን እንፈልጋለን" ያሉ ሲሆን፤ ምላሽ የማይሰጥ ከሆነ ጉዳዩ በሕግ አግባብ የሚታይበት ሁኔታ መኖሩን ጠቁመዋል።

በቅንጅት ውስጥ ካሉ ፓርቲዎች አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) ሊቀመንበር አብረሃም ሃይማኖት በበኩላቸው፤ ፓርቲያቸው ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተለው መሆኑና እንደ ጥምረት በቅርቡ አቋም በመያዝ ይፋ የሚያደርጉ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ለቅንጅቱ በሚደረጉ ጥረቶች እናት ፓርቲ ሌሎች ፓርቲዎች ያቀረቧቸውን ሰነዶች ማቅረቡን አንስተው፤ እገዳው በተለይም ምርጫ በደረሰበት ወቅት መሆኑ በሥራው ላይ መተጓጎል ፈጥሯል ብለዋል።

ሆኖም በጋራና በትብብር መስራቱ የሚቀጥል መሆኑን አቶ አብረሃም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በበኩሉ፤ ከትናንት በስተያ ባወጣው መግለጫ "ከፓርቲው አባላት ቀረበ የተባለው ቅሬታ ሳይደርሰኝ ውሣኔ ተሰጠ" የሚለውን አቤቱታ በተመለከተም ቦርዱ ለሚሰጠው ውሣኔ መሠረታዊ መነሻው የምርጫ ሕጉና የፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ እንዲሁም አስፈላጊ ሲሆን ሌሎች ተገቢነት ያላቸው መረጃዎችን ጭምር በማየት ነው ሲል ገልጿል።

በተያዘው ጉዳይ ቦርዱ በዋናነት ውሣኔውን የሰጠው በዐዋጅ ቁጥር 1162/2011 አንቀጽ 94(3) መሠረት ፓርቲው ለመጣመር አስፋለጊ የሆነውን ውሣኔ ባለማቅረቡ ነው ብሏል።

ይህ ግልጽ የሆነ ዐዋጁን እንዲሁም የፓርቲውን መተዳደሪያ ደንብን የመጣስ ሂዳት ባለበት፤ እንዲሁም ቦርዱ ፓርቲው ምላሽ እንዲሰጠው ጠይቆ የተሰጠውም ምላሽ ከሕግና ከፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ ውጭ መፈጸሙን በግልጽ በመመልከቱ የተሰጠ ውሣኔ ነው ሲል ገልጿል፡፡

ሌሎቹ ለመጣመር ጥያቄ ያቀረቡት አራት ፓርቲዎች ሕጉንና፣ የፓርቲያቸውን መተዳደሪያ ደንብ አክብረው ቦርዱ የጠየቃቸውን ሠነድ አሟልተው እንዲጣመሩ ሲፈቀድላቸው፤ እናት ፓርቲ ግን የራሱን መተዳደሪያ ደንብ፣ የምርጫ ሕጉንና የቦርዱን ውሣኔ ሳያከብር፤ ሕግ በማከበር ጥያቄያቸውን ካቀረቡት ፓርቲዎች ጋር እንዲጣመር መፍቀድ ሕገ-ወጥ የሆኑ አሠራሮች እንዲሠፍኑ ማበረታታት ይሆናል ብሏል።

በተጨማሪም ቦርዱ በትናንትናው እለት ባወጣው መግለጫ፤ ፓርቲው ከአባላት ለሰበሰበው መዋጮ የገንዘብ መቀበያ ደረሰኝ ያለመስጠቱን እና በፓርቲው ስም በሦስት ባንኮች ላይ የሚገኘውን ገንዘብ ትክክለኛነት ማረጋገጥ አለመቻሉ ተገልጿል።

እንዲሁም እናት ፓርቲ ለእርዳታ በሚል ከ158 ሺሕ ብር በላይ መክፈሉን በኦዲት ማረጋገጡንም አስታውቋል፡፡

ስለሆነም ፓርቲው እየተጓዘ ካለበት መንገድ እንዲታቀብ ሲልም ቦርዱ አሳስቧል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ