ጥቅምት 24/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) በማንኛውም ምክንያት ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸውን ተሽከርካሪዎች ከፖሊስ ፈቃድ ሳያገኙ መጠገን፣ ቀለማቸውን መቀየር ወይም ሌላ ማናቸውንም የቀደመ ይዞታቸውን የሚለውጥ ጥገና ማካሄድ በወንጀል እንደሚያስጠይቅ የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት አስታውቋል።

መመሪያውን የሚተላለፉ የተሽከርካሪ ሰርቶ ማሳያ ወርክሾፕ (ጋራዥ) ባለቤቶ ከ20 ሺሕ ብር የገንዘብ መቀጮ ጀምሮ በወንጀል እስከመጠየቅ የሚያደርስ ቅጣት ይጠብቃቸዋል ተብሏል።

ይህ አስገዳጅ መመሪያ ተግባራዊ የተደረገው የትራፊክ አደጋ አድርሰው የሚሰወሩ ወንጀለኞችን ሕገ-ወጥ ድርጊት ለመቆጣጠር እንደሆነ ለአሐዱ የተናገሩት፤ የባለሥልጣኑ የትራፊክ ቁጥጥር እና ሁነት አስተዳደር ዳይሬክተር አቶ አያሌው አቲሳ ናቸው።

አቶ አያሌው የመመሪያውን አስፈላጊነት ሲያብራሩ፤ "ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸው ተሽከርካሪዎች ያለ ፖሊስ እውቅና የቀደመ ይዞታቸውን መለወጣቸው ፖሊስ አደጋ አድርሰው የሚሰወሩ ተሽከርካሪዎችን በቁጥጥር ሥር ለማዋል የሚያደርገውን ጥረት በማደናቀፍ ወንጀለኞች ለጥፋታቸው እንዳይቀጡ እድል ይሰጣል" ብለዋል።

በአስገዳጅ መመሪያው መሠረት ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸውን ተሽከርካሪዎች የሚጠግኑ ጋራዦች በተሽከርካሪው ላይ ምንም አይነት ለውጥ ከማካሄዳቸው በፊት፤ ተሽከርካሪው አደጋ አለማድረሱን እና በፖሊስ እንደማይፈለግ የሚገልጽ ማስረጃ ከፖሊስ መውሰድ ይጠበቅባቸዋል።

ከፍተኛ ጉዳት የደረሰበትን ተሽከርካሪ ያለ ፖሊስ ዕውቅና የሚጠግኑ የጋራጅ ባለንብረቶች በወንጀል እንደሚጠየቁ እና የገንዘብ መቀጮ እንደሚጠብቃቸው፤ የመንገድ ትራንስፖርት ትራፊክ መቆጣጠሪያ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቀጥር 567/2016 ይደነግጋል ሲሉም ዳይሬክተሩ ለአሐዱ ገልጸዋል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ