መስከረም 14/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) በአዋጅ ተቋቁሞ ሥራ ከጀመረ 4 ዓመታትን ያስቆጠረው የፌዴራሊዝም እና የሕገ-መንግሥት አስተምህሮ ማዕከል በባለሙያ እጥረት ምክንያት ሥራውን በአግባቡ ለማከናወን እንደተቸገረ አስታውቋል።

የማዕከሉ ዋና ዳይሬክተር ኃይለየሱስ ታዬ (ዶ/ር) "ለችግሩ መባባስ በምክንያትነት ከሚጠቀሱ ጉዳዮች መካከል ፌደራሊዝምን የሚያስተምሩ ተቋማት ቁጥር አነስተኛ መሆን ዋነኛው ነው" ሲሉ ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡

ዋና ዳይሬክተሩ ማብራሪያቸውን ሲቀጥሉ ትምህርቱ የሚሰጥባቸው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እና የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲም ትምህርቶቹን የሚሰጡት ለሁለተኛ እና ለሦስተኛ ዲግሪ ተማሪዎች ብቻ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

"ከ45 በላይ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ባሉባት ኢትዮጵያ፣ የፌዴራሊዝም ትምህርት በሁለት ዩኒቨርሲቲዎች ብቻ መሰጠቱ ስለጉዳዩ ያለው ግንዛቤ ዝቅተኛ እንዲሆን አድርጓል። ይህ ደግሞ ለማዕከሉ ሥራዎች እንቅፋት እየፈጠረ ነው" ብለዋል፡፡

Post image

ማዕከሉ የተቋቋመው በፌደራሊዝም ዙሪያ ያለውን የአመለካከት ችግር ለመፍታት እንደሆነ ያስታወሱት ዶ/ር ኃይለየሱስ፤ በተለያዩ ሙያዎች ውስጥ ላሉ ሰዎች ማለትም ለጋዜጠኞች፣ ለጸጥታ አካላት፣ ለመንግሥት ሠራተኞች እና ለሌሎች ሙያተኞች በፌዴራሊዝም አስተምህሮ ዙሪያ ስልጠና እየተሰጠ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ተቋሙ ያለውን የባለሙያ እጥረት ለማቃለል ሙያተኞችን ወደ አንድ በማሰባሰብ የባለሙያዎች ማኅበር እስከማቋቋም ድረስ መፍትሄ ለማግኘት እየጣረ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ