መስከረም 14/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሚከበሩትን የመስቀል እና ዘመን መለወጫ በዓላት በመጠቀም፤ የቱሪዝም ገቢን ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ባህል እና ቱሪዝም ቢሮ አስታውቋል።

በመስከረም ወር የተለያየ ስያሜ ተሰጥቷቸው በክልሉ ከሚከበሩ በዓላት መካከል፤ በጉራጌ ዞን "መስቀል"፣ በሀድያ "ያ ሆዴ"፣ በከምባታ ጠንባሮ "መሰላ"፣ እንዲሁም በየም ማኅበረሰብ "ሄቦ" በዓላት እንደሚገኙበት የቢሮው የኮሙኒኬሽን ባለሙያ አቶ በረከት ይገዙ ለአሐዱ ተናግረዋል።

Post image

"በክልሉ ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ ብሔረሰቦች የሚያከብሩት የመስቀል እና የዘመን መለወጫ በዓላት የቱሪዝም መስህብ ናቸው" ያሉት አቶ በረከት፤ በዓላቱ በርካታ ከክልሉ ውጪ የሚኖሩ ተወላጆች ወደ ቀያቸው ተመልሰው ቤተሰቦቻቸውን የሚጠይቁበት ከመሆኑ በተጨማሪ ለሀገር ውስጥ እና ለውጭ ቱሪስቶች መልካም አጋጣሚን የሚፈጥር መሆኑን ገልጸዋል።

Post image

በ2017 ዓ.ም. በነበረው ተመሳሳይ ወቅት ከ755 ሺሕ በላይ የሀገር ውስጥ እና ከ13 ሺሕ በላይ የውጭ ቱሪስቶች ክልሉን መጎብኘታቸውን የገለጹም ሲሆን፤ ከዚህ የቱሪስት ፍሰትም ከ1 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መገኘቱን አስታውሰዋል።

የክልሉ የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ይህንን ስኬት መነሻ በማድረግ፤ የዘንድሮውን የቱሪስት ፍሰት እና ገቢ ለማሳደግ ሰፊ ዝግጅት ስለማድረጉም አብራርተዋል።

ከክብረ በዓሉ ቀን በፊት የተለያዩ የማስተዋወቅ እና የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ስለመሰራታቸውም የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ባህል እና ቱሪዝም ቢሮ አስታውቋል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ