መስከረም 14/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) ትይዩ ካቢኔ ተዋቅሮ ወደ ሥራ መግባቱ ሀገሪቱ እንድትራመድበት በሚፈለገው የልማት ጉዞ ላይ ጉልህ አስተዋፅዖ አድርጓል ሲል የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ) ገልጿል።
ፓርቲው የመንግሥት ሥራዎችን የሚከታተሉ 22 ትይዩ የካቢኔ ሚኒስትሮችን አዋቅሮ ሥራ ማስጀመሩ የሚታወስ ነው።
ይህ ትይዩ ካቢኔ የዕለት ከዕለት የመንግሥት ተግባራትን መከታተል፣ የሚወጡ ረቂቅ ሕጎችን መተቸት፣ የፖሊሲ ንድፈ ሐሳቦችን ማውጣትና መሰል ሥራዎችን ያከናውናል።
አሐዱም ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ "የተቋቋመው ትይዩ ካቢኔ በተገለጸው መሠረት ውጤታማ ሥራዎችን ሰርቷዋል ወይ?" ሲል ጠይቋል።
የኢዜማ ፓርቲ ምክትል መሪና የሕንጻ ንድፍ ባለሙያው አቶ ዮሐንስ መኮንን በሰጡት ምላሽ፤ "ትይዩ ካቢኔው ሀገሪቱ እንድትሄድበት በሚፈልገው የልማት ላይ ጉዞ ጉልህ አስተዋጽኦ አድርጓል" ብለዋል።
ትኩረት በሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች ላይ የፖሊሲ አቅጣጫ ከመስጠት ጀምሮ ሙያዊ ዝርዝር ጥናቶችን በማቅረብ ምክር ሃሳቦችን ለመንግሥት ማቅረቡን አንስተው፤ ከማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ጋር በተያያዘም ጠቃሚ ምልከታዎችን ለመንግሥት እና ለሕዝብም ማቅረቡን ገልጸዋል፡፡
የትይዩ ካቢኔ አባላቱ ፓርቲውን ተፎካካሪ በማድረግ ዋነኛ የሥራ ድርሻቸውን እንደተወጡ የገለጹት ምክትል መሪው፤ 'የኢዜማ አመራሮች እና አባላት ሥልጣን ማግኘታቸው ተፅዕኖ አያሳድርም' በሚል ለሚነሱ ሀሳቦች እንዲህ አይነቱ አካሄድ ሕጋዊ ነው ብለዋል፡፡
በዚህም ትይዩ ካቢኔው መቋቋሙ የመንግሥት ሥራን ለመከታተል ምቹ መደላደል መፍጠሩን ተናግረዋል፡፡
"የካቢኔ አባላት በሕግ አውጪ ወይም በሕግ አስፈጻሚ ውስጥ ቀጥተኛ ተሳትፎ በማድረግ የዴሞክራሲ ስርዓት፣ ሰላምና ልማትን ለማምጣት አስተዋጾ አለው" ያሉ ሲሆን፤ ይህም በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ አዲስ ልምድ በማዳበር ለቀጣይ ምርጫ እራሳችንን እንድናዘጋጅ በቂ ተሞክሮ አግኝተናል ብለዋል።
አያይዘውም የትይዩ ካቢኔ አባላት በሌሎች ዓለም ሀገራት የግድ የፓርቲ አባል መሆን እንደማይጠበቅባቸውና የባለሙያዎችና የሙሁራን ሰብስብ በመሆኑ ለመንግሥት ምክር ሐሳብ ማቅረብ እንደሚችሉ አስታውሰዋል።
መሰል የተቃዋሚ ፓርቲ ትይዩ የካቢኔ ሚኒስትሮች ካሏቸው ሀገራት መካከል እንግሊዝ፣ አውስትራሊያ፣ ካናዳ፣ ፈረንሳይ፣ ጣሊያንና ጃፓን፤ ከአፍሪካም ደቡብ አፍሪካና ሱዳን ተጠቃሽ ናቸው።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
ኢዜማ ትይዩ ካቢኔ ተዋቅሮ ወደ ሥራ መግባቱ ሀገሪቱ እንድትራመድበት በሚፈለገው የልማት ጉዞ ላይ ጉልህ አስተዋፅዖ አድርጓል ሲል ገለጸ
