ጥቅምት 14/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ አገልግሎት መሰጠት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስከ አሁን ድረስ ከ26 ሚሊዮን 500 ሺሕ በላይ ነዋሪዎች መመዝገባቸውን የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ለአሐዱ አስታውቋል።

አብዛኞቹ አገልግሎቶች ከፋይዳ መታወቂያ ጋር እየተሳሰሩ መምጣታቸውን ተከትሎ፤ በርካታ ነዋሪዎች በመታወቂያው ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ ሲሰራ መቆየቱን፤ በብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም የባለድርሻ አካላት እና የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ሳሚናስ ሰይፉ ተናግረዋል።

Post image

የፋይዳ መታወቂያ የፋይናንስ ተቋማትን ጨምሮ በርካታ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ላይ የሚስተዋለውን ማጭበርበርና ሕገ-ወጥ የሆነ አሰራር በመከላከል ከደንበኞቻቸው ጋር መተማመን እንዲኖር የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።

ተቋማት መታወቂያውን በመጠቀም የደንበኞቻቸውን ሙሉ ማንነት ከመለየት ባሻገር የሚኖረውን መተማመንና የአገልግሎት ጥራትን እንደሚያዘምን ተናግረዋል።

ይህ አሰራር የፋይናንስ ስርዓቱ ላይ በተለይም ባንኮች ላይ አዲስ ሂሳብ ማስከፈትን ጨምሮ ተግባራዊ እየሆነ በመምጣቱ ጥሩ የሆኑ ለውጦች መገኘታቸውን ያነሱ ሲሆን፤ በአጠቃላይ እስከ አሁን ባለው ሂደት ከ26 ሚሊዮን 500 ሺሕ በላይ ነዋሪዎች መመዝገባቸውን ገልጸዋል።

ዳይሬክተሩ አያይዘውም በዘንድሮው በጀት ዓመት ማለትም ከሐምሌ 1 ቀን 2017 ዓ.ም እስከ ሰኔ 30 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ 40 ሚሊዮን ተጨማሪ ነዋሪዎችን ለመመዝገብ መታቀዱን አስታውቀዋል።

የዚሁ በጀት ዓመት የመጀመሪያው ሩብ ዓመት መጠናቀቁን በመግለፅ፤ በዚህም ጥሩ የሆነ አፈፃፀም መገኘቱን አመላክተዋል።

በበጀት ዓመቱ አጠቃላይ 40 ሚሊዮን ነዋሪዎችን ለመመዝገብም ከተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ጋር ትስስር በመፍጠር እንዲሁም የማህበረሰቡን ግንዛቤ በማስፋት እየተሰራ እንደሆነ ተናግረዋል።

ይህንንም ተግባራዊ ለማድረግ ነገ ጥቅምት 15 ቅዳሜ እና ጥቅምት 16 ማለትም እሁድ በልዩነት የ12ኛ ክፍል ተማሪዎችንና ግብር ከፋዮችን እንዲሁም ሌሎች የተለያዩ የማህበራዊ አገልግሎት ተጠቃሚውን ህብረተሰብ ታሳቢ ያደረገ የፋይዳ መታወቂያ የምዝገባ ዘመቻ እንደሚካሄድ አስታውቀዋል፡፡

የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተናን ለሚወስዱ ተማሪዎች የፋይዳ መታወቂያን መያዝ ግዴታ መደረጉን ያነሱት ዳይሬክተሩ፤ በመሆኑም በዋናነት እነዚህን ተማሪዎች ጨምሮ የመውጫ ፈተናን (exit exam) የሚወስዱና የሁለተኛ ድግሪ መግቢያ ተፈታኞችን ታሳቢ ያደረገ ዘመቻ እንደሚካሄድ አስታውቀዋል።

በተጨማሪም ፋይዳ መታወቂያ ተግባራዊ ከመደረጉ አስቀድመው የግብር ከፋይ መለያ ቁጥር ያወጡ ግለሰቦችና ተቋማት ከፋይዳ መታወቂያቸው ጋር እንዲያስተሳስሩ ለማድረግ የሚያስችል የኦንላይን አሰራር በቅርቡ ሥራ ላይ እንደዋለ ገልጸዋል።

የሁለት ቀኑ ዘመቻም ከተማሪዎች ባሻገር ይህንን አሰራር የበለጠ ለማጠናከር የሚደረግ እንደሆነ ተናግረዋል።

ከዚህም ሌላ በልዩ ሁኔታ የከተማ ሴፍቲኔት እና የጤና መድህን ተጠቃሚዎችን ለመመዝገብ እና በአጠቃላይ የፋይዳ መታወቂያ ተመዝጋቢዎችን ቁጥር ለመጨመር ታሳቢ ያደረገ ነው ብለዋል።

በዚህም መሰረት ከሰኞ እስከ አርብ ባለው ጊዜ ውስጥ አብዛኛው ሰው ሥራ ላይ እንደሚሆን ከግምት ውስጥ በማስገባት፤ ከሥራ ሰአት ውጪ ቅዳሜና እሁድ በሁሉም የሀገሪቱ ክፍል የሚገኙ የምዝገባ ጣቢያዎች ክፍት ሁነው አገልግሎት እንደሚሰጡ አስታውቀዋል።

የክልል ተቋማትና የከተማ አስተዳደሮችም ህብረተሰቡን መቀስቀስን ጨምሮ ለምዝገባው ስኬት ትብብር እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።

በጊዜያዊነት የቅዳሜና እሁድ ምዝገባ የሚካሄደው ለአንድ ዙር ብቻ መሆኑን ያነሱት ዳይሬክተሩ፤ ወደፊት አፈፃፀሙ ታይቶ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።

ዳይሬክተሩ አክለውም ለሁለት ቀን በሚደረገው ዘመቻ ሁሉም ህብረተሰብ ተጠቃሚ እንዲሆንና ምዝገባውን እንዲያከናውን ጥሪ አቅርበዋል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ