ጥቅምት 14/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) የሚኒስትሮች ምክር ቤት ባካሄደው የመቶ ቀን እቅድ ግምገማ በ2018 የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በ10 ነጥብ 2 በመቶ ያድጋል ተብሎ እንደሚጠበቅ ቅድመ ትንበያ አስቀምጧል፡፡

ምክር ቤቱ የመቶ ቀን እቅድ ግምገማው የዓለምን የኢኮኖሚ አዝማሚያ፣ የኢትዮጵያን ማክሮኢኮኖሚ የመጀመሪያ ሩብ አመት አፈፃፀም እንዲሁም፤ የእድገት አዝማሚያን እና አጠቃላይ ምልከታን ያካተተ አቅርቦትን ያካተተ መሆኑን ገልጿል።

በዚህም በ2017 የበጀት ዓመት የኢትዮጵያ አጠቃላይ የኢኮኖሚ አፈፃፀም በጥንካሬው በመቀጠል፤ 9 ነጥብ 2 በመቶ ዓመታዊ ጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት (ጂዲፒ) ማሳየቱን አስታውቋል።

ይህም 7 ነጥብ 3 በመቶ በሆነ ጠንካራ የግብርና ውጤት መስፋፋት፣ በ13 በመቶ የኢንደስትሪ እድገት ብሎም በ7 ነጥብ 5 በመቶ የአገልግሎት ዘርፍ እድገት የተገለጸ እንደነበር አመላክቷል።

"የኢትዮጵያ የዓመታዊ ጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት (ጂዲፒ) ተዋፅኦም በብዝኃ መሠረት እየያዘ መሄዱን የሚያሳይ ነው" ያለው ምክር ቤቱ፤ ይህም በግብርና 31 ነጥብ 3 በመቶ፣ በኢንደስትሪ 30 ነጥብ 2 በመቶ እና በአገልግሎት 39 ነጥብ 6 በመቶ አስተዋፅኦ የታየበት መሆኑን ነው የገለጸው።

እየተካሄዱ በሚገኙ የለውጥ ሥራዎች፣ በመንግሥት እየተከወኑ ባሉ የተለያዩ የልማት ሥራዎች እና አዲስ ኢንቨስትመንቶች በመደገፍ፤ በ2018 ዓመተ ምኅረት ኢኮኖሚው በ10 ነጥብ 2 በመቶ ያድጋል ተብሎ እንደሚጠበቅም አስታውቋል።

እንደ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ያሉ ፕሮጀክቶች መጠናቀቅ ብሎም እንደ የማዳበሪያ ማምረቻ እና የተፈጥሮ ጋዝ ልማት ሥራ ጅማሮዎች የኢኮኖሚ እድገቱን የበለጠ ያነቃቁታል ተብሎ እንደሚጠበቅም አመላክቷል።

ግብርና በ7 ነጥብ 8 በመቶ፣ በአዳዲስ የማኑፋክቸሪንግ ፕሮጀክቶች እና የተሻሻሉ ግብዓቶች የተጠናከረው ኢንደስትሪ 13 ነጥብ 2 በመቶ እንደሚያድጉ የተተነበየ ሲሆን፤ ማዕድን ለ2018 የተቀመጠለትን ግብ እንደሚበልጥ ይጠበቃል ተብሏል።

በተጨማሪም የአገልግሎት ዘርፉ እድገት በሚያሳዩት የንግድ እንቅስቃሴ፣ የትራንስፖርት አገልግሎት፣ የቱሪዝም ፍሰት እና የዲጂታል ኢኮኖሚ መስፋፋት በመጠቀም 9 ነጥብ 3 በመቶ እድገት እንደሚጠበቅ ተገልጿል።

የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎትም በሶስት ወራት ብቻ 6 ነጥብ 5 ትሪሊዮን ብር የተንቀሳቀሰበት ደረጃ መድረሱን ያስታወቀው ምክት ቤቱ፤ የውጭ ንግድ 2 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር መድረሱን ይህም እቅዱን እና የባለፈውን ዓመት ተመሳሳይ ጊዜ አፈፃፀም የበለጠ ሆኖ መታየቱን አስታውቋል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ