ጥቅምት 5/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) በ2018 ዓ.ም ለሚካሄደው 7ኛው ሀገራዊ ምርጫ "የምርጫ ቅስቀሳ ለማካሄድ የሚያስችል ሁኔታ የለም" ሲሉ እናት እና ኢዜማ ፓርቲ ለአሐዱ ገልጸዋል።

የፓርቲዎቹ ተወካዮች በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ያለው የጸጥታ ችግር የምርጫ ቅስቀሳውን "ሊያስተጓጉል ይችላል" ብለዋል። መንግሥት ሰላምና ማረጋገጥ እና የፖለቲካ ሂደቱ ላይ ጫና የሚያሳድሩ ጉዳዮችን እንዲያስተካክልም ጠይቀዋል፡፡

የእናት ፓርቲ ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ጌትነት ወርቁ፤ "ፓርቲዎች በክልል ከተሞች የምርጫ ቅስቀሳ ለማድረግ የሚያስችል ሁኔታ አለ ለማለት ባይቻልም፡፡ መንግሥት የፖለቲካ ምኅዳሩን በማስፋት ነጻ የመገናኝ ብዙኃን ውይይት እንዲኖር መፍቀድ አለበት" ብለዋል

አሁን ባለው የጸጥታ ችግር ሀገራዊ ፓርቲዎች በመላው ኢትዮጵያ እንደልብ ተንቀሳቅሰው ሃሳባቸውን ገልጸው ለምርጫ የሚቀሰቅሱበት አስቻይ ሁኔታ እንደሌለ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ኢዩኤል ሰሎሞን በበኩላቸው፤ 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ የሰሜኑን ጦርነት እና በሌሎችም ግጭቶች ምክንያት በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የተካሄደ እንደነበር አስታውሰው፤ 7ኛው ሀገራዊ ምርጫም በየአካባቢው እያጋጠሙ ባሉ ግጭቶች ምክንያት "አስቻይ ሁኔታ ይኖራል ማለት እንደማይቻልም" ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የ2018ዓ.ም የሚካሄደው 7ኛው ሀገራዊ ምርጫ በተሳካ ሁኔታ እንዲከናወን ሰፊ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን፤ ለመገናኛ ብዙኃን በሰጠው መግለጫ ማስታወቁ ይታወሳል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ