ጥቅምት 5/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) በውጭ ሃይሎች ሀገሪቱ ላይ እየተቃጣ ያለው ወረራ የተፈጥሮ ሀብቷን ለመቆጣጠር ያለመ ነው ሲሉ በኢትዮጵያ የቬንዙዌላ አምባሳደር የሆኑት ኤዲ ኮርዶቫ ገልጸዋል።

አምባሳደር ኮርዶቫ በኢትዮጵያ ያለውን ጨምሮ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ወደ 120 የሚሆኑ የቬንዙዌላ ኤምባሲዎች አሜሪካ በቬንዙዌላ ላይ የደቀነቸውንና እያደገ የመጣውን ስጋት አስመልክቶ የሀገሪቱን እውነት የማሳወቅ ሥራ እየሰሩ ነው" ሲሉ ለአሐዱ የገለጹ ሲሆን፤ በውጭ ሃይሎች እየተቃጣ ያለው ወረራ የቬንዙዌላ የተፈጥሮ ሀብት ለመቆጣጠር በማቀድ ነው ብለዋል፡፡

ይህ አሁን 'የፀረ አደንዛዥ እፅ ትግል' በሚል ሽፋን አሜሪካና አጋሮቿ በቬንዙዌላ ላይ እያደረሱት ያለው ጫና ባለፉት 26 ዓመታት ተጠናክሮ የቀጠለ ነው ሲሉም አምሳደሩ ተናግረዋል፡፡

ቬንዙዌላ በተፈጥሮ ሀብት የታደለች መሆኗን የጠቆሙት አምሳደር ኮርዶቫ፤ ከዓለም አጠቃላይ የነዳጅ ሀብት 19 በመቶ ድርሻ አላት ብለዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በዓለም ላይ 4ኛዋ ከፍተኛ የጋዝ ክምችት ባለቤትና እና 2ኛዋ ከፍተኛ የወርቅ ማእድን ባለፀጋ ናት ሲሉ አብራርተዋል፡፡
በዚህም "አሜሪካ በተለያዩ ዘርፎች ላይ ከፍተኛ ተፅእኖ እያሳደረች ነው" ያሉት አምባሳደሩ፤ በሀገሪቱ ላይ ከ1 ሺሕ 400 በላይ ማዕቀቦች እንደተጣሉባት አንስተዋል፡፡

በተለይም ከ10 ዓመታት በፊት የአሜሪካ መንግሥት ቬነዝዌላን ጠላት ብሎ ከፈረጀ በኋላ ጫናዎች የበለጠ እየጠነከሩ መምጣታቸውን ነው አምባሳደሩ ያስረዱት፡፡

ይህንን ተከትሎም ቬንዙዌላ በተለያዩ ዓለማቀፍ ተቋማት የነበራት 20 ቢሊዮን ዶላር ያላግባብ ተይዞባታል፣ የሀገሪቱ ገንዘብም ከዶላር አንጻር ያለው ምንዛሬ እንዲያሽቆለቁል ተፅእኖ ተደርጎባታል ብለዋል፡፡

"ከአውሮፓውኑ 2015 ጀምሮ ባሉት ሰባት ተከታታታይ ዓመታት ወደ 40 ቢሊዮን ዶላር የቬንዙዌላ መንግሥትና ሕዝብ ኪሳራ ደርሶበታል" ሲሉ የማዕቀቦቹን ተፅእኖ የገለጹት አምባሳደሩ፤ በ2015 እና በ2020 መካከል የሀገሪቱ የነዳጅ ሽያጭ በ87 በመቶ እንዲቀንስ ማድረጉን ለአሐዱ አስረድተዋል፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ሃላፊዋ ባስጠኑት ጥናት፤ በቬንዙዌላ ላይ የተጣሉት ማዕቀቦች የሀገሪቱን ሕዝብ በከፍተኛ ሁኔታ እየጎዱ መሆናቸውን ተናግረዋል ብለዋል፡፡

ጫናው ባለፉት 3 ዓመታት ደግሞ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መምጣቱን የገለጹም ሲሆን፤ "አሁን ደግሞ በአሜሪካ በኩል በሀገሪቱ ላይ ትልቅ ወታደራዊ ስጋት ተደቅኖብናል፡፡ ይህ አይነቱ ሁኔታም ቬንዙዌላን ብቻ ሳይሆን በአካባቢው የሚገኙ የካሪቢያን ሀገራትን አደጋ ላይ የሚጥል ጭምር ነው" ብለዋል፡፡

የውጭ ሃይሎች ወረራቸውን ምክንያታዊ ለማድረግም የተለያዩ ሽፋኖችን በማቅረብ የተፈጥሮ ሀብቷን ለመቆጣጠርን ጥረት እየተደረገ ነው ሲሉ ድርጊቱን ኮንነዋል፡፡

የዋሽንግተን መንግሥትም የዓለም አቀፍ ሕግን በመጣስ በዓለማቀፍ ውሃ ላይ በጀልባ የሚንቀሳቀሱ ሰዎችን በመግደል ከፍርድ ውጭ የሆኑ ግድያዎችን ፈፅሟል፤ ዘመናዊ የF – 35 ጀቶችን፣ በአየር፣ በባህር ላይ 4 ሺሕ እስከ 4 ሺሕ 500 የሚሆኑ ወታደሮችን የያዙ ሰርጓጅ መርከቦችን ወደ ቬነዝዌላ አስጠግቷል ሲሉ ገልጸዋል፡፡

"የቬንዙዌላ አሳ አጥማጆችን የአሜሪካ ወታደሮች እየያዙ ነው" ያሉት አምባሳደር ኮርዶቫ፤ አምስት የF- 35 የጦር ጀቶች የቬንዙዌላን የባህር ክልል ጥሰው ገብተው ዝቅ ብለው በመብረር ቬንዙዌላን ለጦርንት እየጋበዙ ነው ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል "ቬንዙዌላን ከእፅ ዝውውር ጋር በተያያዘ ያላት ድርሻ በጣም ዝቅተኛና የፕሬዝደንት ኒኮላስ ማዱሮ መንግሥትም ከፍተኛ የመከላከል ሥራ እየሰራ ባለበት ሁኔታ፤ የዋሽንግተን መንግሥት ግን ያለበቂ ማስረጃ ሀገሪቱን እየወነጀለ ነው" ብለዋል፡፡

ከዚህ ባሻገርም "የፕሬዝደንት ትራምፕ መንግሥት በቬንዙዌላ የመንግሥት ለውጥ እንዲደረግ ይፈልጋል" ያሉ ሲሆን፤ በሀገሪቱ የዲሞክራሲ ስርዓት እንዲያድግ የሚያደርግ አሳታፊ የሆነ ምርጫ በየጊዜው እየተካሄደ ነው ሲሉ አፅንዖት ሰጥተውበታል፡፡

በዚህም በ26 ዓመታት ውስጥ 33 ጊዜ ምርጫ ተደርጓል፤ ይህንን እና ተያያዥ የቬንዙዌላን እውነታዎች ለዓለም እያሳወቅን እንገኛለን ያሉት አምባደር ኮርዶቫ፤ ሀገሪቱ ለሚሰነዘርባት ጥቃት ዓለም አቀፍ ሕግችን መሰረት በማድረግ አስፈላጊውን ራስን የመከላከል ሥራም ትሰራለች ብለዋል፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ