ጥቅምት 5/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) 10ኛው የኢትዮጵያ ከተሞች ፎረም "የከተሞች እድገት ለኢትዮጵያ ልህቀት" በሚል መሪ ቃል በአፋር ክልል ሰመራ ሎጊያ ከተማ ከሕዳር 6 እስከ 10 ቀን 2018 ዓ.ም እንደሚካሄድ የከተማና መሰረተ-ልማት ሚኒስቴር ማስታወቁ ይታወሳል።

ከተሞች በዚህ ፎረም ተሳታፊ ለመሆንም እስከ መስከረም 30 ድረስ ምዝገባ ማጠናቀቅ እንደሚገባቸው መግለፁም አይዘነጋም።

ነገር ግን የምዝገባው ጊዜ እስከ ጥቅምት 15 ቀን 2018 ዓ.ም መራዘሙን የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የሕዝብ ግንኙነት እና ኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈጻሚ አቶ ኢትዮጵያ በዴቻ ለአሐዱ ተናግረዋል።

በፎረሙ የሚሳተፉ ከተሞች መመዝገቢያ ጊዜ የተራዘመበት አንዱ ምክንያት አንዳንድ ከተሞች ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን ተከትሎ እድል ለመስጠት እንደሆነ ገልጸዋል።

ፎረሙ በከተማና መሰረተ ልማት ዘርፍ አፈጻጸም ላይ የከተማ ነዋሪዎችን፣ የመንግሥትና ሌሎች ባለድርሻ አካላትን ተሳትፎ እና ትብብር በማጠናከር መልካም ተሞክሮዎችንና ልምዶችን ለማስፋፋት የሚያስችል መሆኑ ተገልጿል።

በፎረሙም የከተሞች ልምድ ልውውጥ እና የከተሞችን እድገት በተመለከተ በተለያዩ ምሁራንና ባለሙያዎች የፓናል ውይይት እንደሚካሄድ ተጠቁሟል።

በዚህ ፎረሙ ከ150 በላይ ከተሞች እና ከ10 በላይ ድርጅቶች ይሳተፋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ከተሞች ፎረም በ2002 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ የተጀመረ ሲሆን፤ ከአሁን ቀደም በተለያዩ ከተሞች ለ9 ዙሮች ተካሂዷል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ