ሰኔ 24/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የጤና ባለሙያዎች ከወራት በፊት ደመወዝን ጨምሮ በርካታ ጥያቄዎችን በማንሳት ከመንግሥት በኩል ምላሽ እንዲሰጣቸው ያቀረቡት ጥያቄ፤ ምላሽ እንደሚያገኝ እምነት እንዳለው የኢትዮጵያ ጤና ባለሙያዎች ማህበር ገልጿል፡፡
የጤና ባለሙያዎች ከተመጣጣኝ ደመወዝ፣ ከጥቅማጥቅም፣ ከሙያ እድገት ዕድሎች እንዲሁም ከምቹ የሥራ ቦታ እና የሥራ ቦታ ነጻነት ጋር የተያያዙ ባለ 12 ነጥብ ጥያቄዎችን ሚያዝያ 3 ቀን 2017 ዓ.ም. ለጤና ሚኒስቴር ማቅረባቸው የሚታወስ ሲሆን፤ በዚህም 'መንግሥት እነዚህን ጥያቄዎች በተሰጠው 30 ቀናት አልፈጸመም' በሚል ከግንቦት 5 ጀምሮ ለአንድ ወር የሚቆይ የሥራ ማቆም አድማ ማድረጋቸው ይታወቃል።
ከሰሞኑም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከፖለቲከኞች፣ መምህራን፣ የሃይማኖት ተቋማት ጋር ውይይት ያደረጉ ሲሆን፤ ጥያቄያቸውን ሲያቀርቡ ከቆዩት የጤና ባለሙያዎች ጋርም ውይይት አድርገዋል።
በውይይቱ ላይም "የጤና ባለሙያዎች ጥያቄ የፖለቲካ ፍላጎት ባላቸው አካላት ተጠልፎ ከባለሙያዎች እጅ ወጥቷል" ሲሉም ጠ/ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
"የጤና ባለሙያዎች ጥያቄ በራሳቸው በጤና ባለሙያዎች ተነሳሽነት የተጀመረ ነው" የሚሉት የኢትዮጵያ ጤና ባለሙያዎች ማህበር ፕሬዝዳንት ዶ/ር ዮናታን ዳኘው፤ "የጤና ባለሙያዎች እንቅስቃሴን ፖለቲከኞች በተለያየ አውድ ቢወስዱትም 'ዋናው መሠረቱ ምንድን ነው?' የሚለውን በማየት ችግሩ መሬት ላይ ያለ መሆኑን መረዳት ይቻላል" ብለዋል።
"በውይይቱ ወቅት የጤና ባለሙያው ጥያቄ እና ያለበት ጫና በደንብ አልተነሳም" ያሉም ሲሆን፤ ነገር ግን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በውይይቱ ወቅት ባስቀመጧቸው አቅጣጫዎች ችግሩ ይፈታል የሚል እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል።
ነገር ግን ይኸው የጤና ባለሙያዎች ጥያቄ ምላሽ የማያገኝ ከሆነ ጥያቄው በድጋሜ የሚነሳበት ሁኔታ መኖሩን ጠቁመዋል።
የጤና ባለሙያዎች ያነሱትን የመብት ጥያቄ ሽፋን በማድረግ "በሀገሪቱ ትርምስ እንዲፈጠር ከሚሠሩ ኃይሎች ጋር በማበር ሕገ ወጥ የሥራ ማቆም አድማ በማድረግ፤ በጤና ዘርፉ ላይ ሁከት በመፍጠር እና የታካሚዎችን ሕይወት አደጋ ላይ በመጣል የተጠረጠሩ" 47 የጤና ባለሙያዎችን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በቁጥጥር ሥር አውሎ ምርመራ ማጣራት መጀመሩን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ መግለጽ ይታወቃል።
ይህንን ተከትሎም የማህበሩ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ዮናታን፤ አሁን ላይ ባለው መረጃ መሠረት በእስር ላይ ከነበሩት የጤና ባለሙያዎች የተለቀቁ መኖራቸውን አንስተዋል።
የደመወዝ፣ የጥቅማጥቅም፣ የጤና ባለሙያ ሕክምና ከተለያዩ ታካሚዎች ጋር የሚገናኝ መሆኑን ተከትሎ ለተላላፊ በሽታዎች ተጋላጭ በመሆኑ፤ የተጋላጭነት ክፍያ እና የጤና ባለሙያዎች የጤና ኢንሹራንሽ የጤና ባለሙያዎች ያነሷቸው ጥያቄዎቹ ዋንኞቹ ናቸው።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
የጤና ባለሙያዎች ጥያቄ ምላሽ እንደሚያገኝ እምነት እንዳለው የኢትዮጵያ ጤና ባለሙያዎች ማህበር ገለጸ
