የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በ2018 ዓ.ም. በሚያካሂደው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ላይ የሚፊካከሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች እጩዎቻቸውን ቦርዱ ባበለጸገው ሥርዓት ተጠቅመው እንዲያስመዘግቡ ጥሪ ማቅረብ ከጀመረ ሰንበት ብሏል።
ፓርቲዎች የመሙያ ቅጾችን በማውረድ ከተጠየቀው ከሕዳር 8 እስከ ሕዳር 23 ቀን 2018 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ውስጥ በቦርዱ ዋና መሥሪያ ቤት በአካል በመገኘት ሠነዱን እንዲያቀርቡ ተገልጿል።
በተጨማሪም ቦርዱ በ6ኛው ጠቅላላ ምርጫ የተወዳደሩ ፖለቲካ ፓርቲዎች ለውድድር የተጠቀሙባቸውን መወዳደሪያ ምልክቶች ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የመጠቀም ቀዳሚ መብት እንዳላቸው አስገንዝቧል።

ፓርቲዎች ሕጋዊ አካሄድን የተከተለ መንገድ የራሳቸውን የመወዳደሪያ ምልክት ማቅረብ የሚችሉ ሲሆን፤ በአማራጭም ቦርዱ ከሚያቀርበው የመወዳደሪያ ምልክት ዝርዝር ውስጥ መምረጥ እንደሚችሉ ተነግሯል።
የግል ዕጩዎች ምዝገባ ደግሞ ቦርዱ ባበለጸገው መተግበሪያ የሚከናወን ሲሆን፤ የሚጀመርበት ጊዜ በቀጣይ ይፋ የሚደረግ ይሆናል።
ይሁን እንጂ ቦርዱ ያስቀመጠው የጊዜ ገደብ በትናንትናው ዕለት መጠናቀቁን ተከትሎ፤ በተለያዩ ፓርቲዎች በኩል ቅሬታዎች ሲቀርቡ ተደምጧል። ቦርዱም ከፓርቲዎቹ በቀረበ ጥያቄ መሠረት የጊዜ ሰሌዳው ጊዜያዊ እንደመሆኑ መጠን ቀነ ገደቡን እንደሚያራዝመውና ፓርቲዎቹም መረጃዎችን ለቦርዱ የማቅረብ ሥራ እንዲቀጥሉ መገለጹ ተነግሯል።
ቦርዱ ከፓርቲዎች ተደጋጋሚ መግለጫዎችና ቅሬታዎች ሳይገታ፤ የእጩ ምዝገባ እንዲሁም ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የሚሳተፉ የምርጫ ክልል አስፈጻሚዎች የብቃት ማረጋገጫ ምዘና ፈተና መስጠቱን ቀጥሏል።
እስካሁን ድረስ ይህንን ቀነ ገደብ በመጠቀም ዕጩ ካስመዘገቡ ጥቂት ፓርቲዎች መካከል የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ይገኝበታል። ይሁን እንጂ ፓርቲው ዕጩ ያስመዘገበው በአዲስ አበባ የምርጫ ክልሎች ብቻ መሆኑን የገለጸ ሲሆን፤ “በሌሎች አካባቢዎች አስቻይ ሁኔታ ባለመኖሩ የመወዳደር ፍላጎት የለንም” ሲሉ የፓርቲው ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ሙላት ገመቹ ለአሐዱ ተናግረዋል።

የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ከሰሞኑ ባደረጉት አስቸኳይ ስብሰባ፣ ስለ 7ኛ ዙር ጠቅላላ ምርጫ ተሳትፎን በተመለከተ በደረሱበት ውሳኔ መሠረት ኦፌኮ በመጪው አጠቃላይ ምርጫ ‘ምሳሌያዊና ስልታዊ ተሳትፎ’ የተሰኘ ስትራቴጂን በመከተል፤ በአዲስ አበባ (ፊንፊኔ) የምርጫ ክልሎች ላይ እና የደኅንነት ሁኔታው ለምርጫ ለመሳተፍ አስቻይ መሆኑን የሥራ አስፈጻሚው ገምግሞ በሚያጸድቃቸው የምርጫ ክልሎች ብቻ ዕጩዎቹን እንዲያቀርብ መወሰኑን በመግለጫ አስታውቋል።
ፓርቲው ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ሙላት ገመቹ፤ መመረጥ በምንችልበት ቦታ ላይ ብቻ ነው የምንወዳደረው ሲሉ ገልጸዋል።
"በመሆኑም አስቻይ ሁኔታ አለበት በሚባለው ከተማ ላይ ብቻ ምርጫ ለማድረግ እንገደዳለን ያሉ ሲሆን፤ የ6ኛ ዙር ምርጫ እንዳለፈን ሁሉን ያሁኑም እንዳያልፈን በሚል የሚደረግ ምርጫ ነው" ሲሉም አስረድተዋል።
ሌሎች ፓርቲዎችም በሀገሪቱ ሰላም እጦት ምክንያት ምርጫውን በተመለከተ ሥጋታቸውን ገልጸዋል። የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ሊቀመንበር አቶ አብርሐም ጌጡ በበኩላቸው፤ ስለ ምርጫ ከማሰባችን በፊት የሀገሪቱ ሕዝብ በምን ሁኔታ ላይ ነው ያለው የሚለውን መመልከት አለብን ብለዋል።

"በኢትዮጵያ በተለያዩ የሀገሪቱ አቅጣጫዎች ያሉ አለመረጋጋቶች እና ቀውሶች ከምርጫው በፊት መፈታት እንዳለበት ለመንግሥት በተደጋጋሚ ጊዜ ስንገልጽ ቆይተናል። አሁንም ጥሪያችን ይህ ነው" ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።
አቶ አብርሐም ጌጡ፤ አሁን ላይ በሁሉም ሁኔታ ላይ ምርጫ ስለመደረጉ እና የምርጫ ዝግጅት ከመነጋገራችን አስቀድመን በፖለቲካ እሳቤያቸው የታሠሩ ፖለቲከኞች እና ጋዜጠኞች እንዲፈቱ ሲሉም ጠይቀዋል።
"ችግሮች ወደፊት አውጥተን ተወያይተን መፍትሔ መስጠት ይገባል። እነዚህ ችግሮች ሳይፈቱ ምርጫ ማከናወን አይታሰብም" ሲሉም ጨምረው ተናግረዋል። ምርጫው ተዓማኒ መሆንና ሁሉም በነፃነት የሚሳተፍበት እንዲሆን ከተፈለገ መንግሥት ለሰላሙ ኃላፊነቱን መውሰድ ይኖርበታል ሲሉም አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) የውጭ ጉዳይ ኃላፊ አቶ እስክንድር ሞገስ ከእጩ ምዝገባው ጋር በተያያዘ ቦርዱ ሐሳቡን በራሱ ጊዜ እየቀያየረ ይገኛል ሲሉ ወቅሰዋል።

"ከዚህ ቀደም ፓርቲዎች ሁሉ በተገኙበት የተወሰነውን እጩ ምዝገባ ቀነ ገደብ በራሱ በመቀየር እስከ ሕዳር 23 በሚል ማስቀመጡ ተገቢ አለመሆኑን በማሳወቅ፤ ለቦርዱ ደብዳቤ አስገብተናል። ቦርዱ በፈለገው ጊዜ በሚቀያይረው ቀነ ገደብ ሁሉ መሳተፍ ለምርጫው አጃቢ ከመሆን የዘለለ የሚፈይደው ነገር አይኖርም" ሲሉ አስረድተዋል።
ይሁን እንጂ ምርጫ ቦርድ የእጩ ምዝገባ ቀነ ገደቡ መራዘሙን ሲያስታውቅ፤ ፓርቲዎች አሁንም መረጃዎቻቸውን እንዲያቀርቡ እየጠየቀ ይገኛል። የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) ዕጩዎቹን በሁሉም የሀገሪቱ ክልሎች የማስመዝገብ ፍላጎት እንዳለው ገልጿል።
"ይሁን እንጂ አስቻይ ሁኔታ አሁንም አለ ብሎ እንደማያምን የገለጹት አቶ እስክንድር፣ መንግሥት አሁንም ሰላሙን ለማምጣት ኃላፊነቱን ሊወስድ ይገባል" ሲሉ በአጽንዖት ተናግረዋል።
ምርጫ ለማድረግ አስቻይነት ጥያቄ ከሚነሳባቸው አካባቢዎች አንዱና ዋነኛው የትግራይ ክልል መሆኑ ይጠቀሳል። በተለይም በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች በተደጋጋሚ የሚያነሱት የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት አለመከበር ለምርጫ አስቻይ ሁኔታ እንዳይፈጠር ማድረጉን ነው። ከሰሞኑም ሕዝባዊ ወያነ ሐርነት ትግራይ (ሕወሓት) ባወጣው መግለጫ፤ ድርጅቱ ሕጋዊ ዕውቅናው ሳይመለስ በትግራይ ምንም ዓይነት ምርጫ አይከናወንም ማለቱ ይታወሳል።
ይህም በክልሉ የሚኖረውን የምርጫ ሂደት ውስብስብ እያደረገው ሲሆን፤ የትግራይ ነፃነት ፓርቲ ሊቀመንበር ደጀን መዝገቦ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ምርጫ ቦርድ በትግራይ ክልል የቅድመ ዝግጅት ሥራውን በሚገባ እየሰራ አለመሆኑን ተናግረዋል።

"ከቦርዱ ጋር ተደጋጋሚ ንግግር ሲደረግ መቆየቱን የገለጹ ሲሆን፤ "በክልሉ ምርጫ አስቻይ የሚባል ሁኔታ አለ" ለማለት እንደማያስችል መግለጻቸውን ተናግረዋል። "ይህም በሕወሓት ምርጫ ማድረግ አይቻልም በማለቱ ሳይሆን፣ በክልሉ ከድኅረ ጦርነት በኋላ መከናወን የነበረባቸው ሥራዎች አለመሰራታቸው ነው" ሲሉ ጨምረው ገልጸዋል።
"ክልሉ ከፌዴራል መንግሥት ጋር በሚገባው መንገድ ተዋህዷል ማለት አያስደፍርም" የሚሉት ዶክተር ደጀን፣ ምንም ዓይነት ትግራይ የለውም ይላሉ። በዚህም "ምርጫ ለማድረግ በፓርቲያቸው በኩል ፍላጎት ቢኖርም አስቻይ ሁኔታ መከወን አልተቻለም" ሲሉ ገልጸዋል።
ሊቀመንበሩ አሁንም በክልሉ ምርጫ ለማከናወን የፕሪቶሪያው ሰላም ስምምነት የመሰሉ ጉዳዮች ተፈጻሚ መሆን ይገባቸዋል ብለዋል።
በመጨረሻም፣ በሀገሪቱ ያሉ አለመረጋጋቶች መፍትሔ እንዲሰጣቸው ፓርቲዎቹ ያሳሰቡ ሲሆን፣ ይህ የሚሆን ከሆነ ሰላማዊ እና ተዓማኒ ምርጫ ለማድረግ ያስችላል ይላሉ።
በተጨማሪም ቦርዱ "ራሱ ለሚያወጣው የጊዜ ሠሌዳ ታማኝ መሆን ይኖርበታል" የተባለ ሲሆን፤ ይህም የእጩ ምርጫውን ያራዘመበት መንገድ ምላሽ እንዲሰጥ ተጠይቋል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ