የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምክክር ኮሚሽን የተቋቋመበት አዋጅ ቁጥር 1265/2014 አካታችነትን የብሔራዊ ምክክሩ መጀመሪያና ዋነኛ መርህ አድርጎ ደንግጓል።

ብሔራዊ ምክክር በተለያየ ጎራ የተሰለፉ የሐሳብ መሪዎችንና ቡድኖችን ወደ አንድ ጠረጴዛ በማምጣት፤ በወሳኝ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ይመክራል። በመሆኑም ምክክሩ ተመሳሳይ አቋም በመያዝ እንደ አገር መዋቅራዊ ለውጥ ለማምጣት የሚረዳ መሳሪያ መሆኑ ይገለጻል።

በዓለም ዙሪያ ባሉ ሀገሮች የብሔራዊ ምክክር የተለያዩ ስያሜዎች ሊኖሩት ቢችሉም፤ የዝግጅት፣ የሂደትና የትግበራ የሚሉ ምዕራፎችን ማለፉ ግን አንድ ያደርገዋል።

በርካታ የዓለም አገሮች ከጦርነትና ከሌሎች ችግሮች በኋላ፤ ወደ ግጭት የወሰዷቸውንና አላግባባ ያሏቸውን ጉዳዮች በሰለጠነ መንገድ በንግግር ለመፍታት ብሔራዊ ውይይት ማድረጋቸውን ሰነዶች ያስረዳሉ።

በኢትዮጵያም በተለይም በፖለቲካ እና በሐሳብ መሪዎች እንዲሁም በሕብረተሰብ ክፍሎች መካከል ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን ልዩነት መፍታት፤ ለሀገራዊ አንድነት መሠረት መሆኑ ይገለጻል። በመሆኑም፤ ይህንን አካታች ውይይት ለማድረግ ብሔራዊ የምክክር ኮሚሽን ተቋቁሞ ውይይቱን በማስተባበር ላይ ይገኛል።

Post image

የብሔራዊ ምክክር ኮሚሽኑ አሁንም ድረስ የትግራይ ክልል ታጣቂዎችን እና በማረሚያ ቤት ያሉ ዜጎችን በምክክሩ ሂደት ላይ ማካተት እንዳለበት በተደጋጋሚ ይገለጻል።

ከአሥራ አንድ ኮሚሽነሮች መካከል አንዱ የሆኑት ኮሚሽነር አምባዬ ኡጋቶ፤ ኮሚሽኑ ከተቋቋመ ጀምሮ አካታችነትን በመሠረታዊነት እንደያዘ ያነሳሉ።

"ችግሮቻችንን ወደ ውስጥ ስንመለከት በዋናነት ያለው ችግር ያለማካተት በመሆኑ፤ ኮሚሽኑ ይህንን ለመቅረፍ የተለያዩ መንገዶችን በመጠቀም አካታች ለመሆን እየሰራ ይገኛል" ሲሉም ተናግረዋል።

በዚህ ሂደት ከአካታችነት ጋር በተያያዘ የትግራይ ክልል ዋነኛው ጉዳይ መሆኑ የሚገለጽ ሲሆን፤ ኮሚሽኑ የሞከራቸው ሁሉም ሙከራዎች እስካሁን ውጤታማ እየሆኑለት አይደሉም።

ኮሚሽኑ ከተለያዩ የክልሉ ምሁራን እና የመንግሥት አካላት ጋር በርካታ ውይይቶችን ያደረገ ቢሆንም፤ ወደ ወጤት ባለመምጣቱ 'አጀንዳ ማሰባሰብ' የሚለው ሥራ መጀመር አልተቻለም።

Post image

ኮሚሽነር አምባዬ ኡጋቶ ይህንን በሚመለከት ከፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ወዲህ በርካታ ውይይት ቢደረግም ሊሳካ አለመቻሉን ገልጸዋል። "ነገር ግን ኮሚሽኑ አካታችነት እውን ለማድረግ የትግራይ ሕዝብ በዚህ ሂደት መሳተፍ ግድ ይኖርበታል" ሲሉም አብራርተዋል።

የብሔራዊ ምክክር ኮሚሽን ከአካታችነት ጋር የሚገጥሙትን ችግሮች ለመፍታት በተለይም ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ጋር በጋራ ሲሰራ ቆይቷል።

የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ከፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ከትግራይ ክልል እና ከታጣቂዎች ጋር ያሉ ችግሮች ለመፍታት ጥረት ሲያደርግ መቆየቱን ይገልጻል።

የምክር ቤቱ የሕግና ፖሊሲ ጉዳዮች ዳይሬክተር ዘላለም እሸቱ በበኩላቸው፤ ከኮሚሽኑ የራቁ አካላትን ወደ ምክክሩ እንዲቀርቡ የማድረግ ሥራ ሲሰሩ መቆየታቸውን ይናገራሉ። ይህንን የአካታችነት ችግር በመለየት ሥራዎችን እየሰሩ እንደሚገኙና የማስታረቅ ሥራዎችም አሁንም እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል።

Post image

ከአካታችነት ጋር በተያያዘ በኮሚሽኑ ላይ ቅሬታ ከሚያቀርቡ አካላት መካከል ሴቶች እና የአካል ጉዳተኞች ማኅበራት ይገኙበታል።

ይህንን በሚመለከት አቶ ዘላለም እሸቱ ሲያስረዱ፤ ኮሚሽኑ በሂደት አካታች እየሆነ መምጣቱን ይናገራሉ። በተለይም ከሴቶች እና አካል ጉዳተኞች ጋር የነበሩ ችግሮችን እየፈታ መምጣቱን ያነሱ ሲሆን፤ ማኅበራቱ አጀንዳቸውን ወደ ፊት ለማምጣትም መደገፋቸውንም አብራርተዋል።

ሌላው ኮሚሽኑ በተደጋጋሚ ጥያቄ ሲቀርብለት የነበረው 'በሕግ ጥላ ስር ያሉ ዜጎችን አጀንዳ ማሰባሰብ ስራውን መስራት አለበት' የሚል ነበር። ኮሚሽነር አምባዬ ኡጋቶ ይህንን ሥራ በቀጣይ ሳምንት ጀምሮ እንደሚሰራበት ተናግረዋል። መስተካከል ያለባቸው ከአካታችነት ጋር ጥያቄ የሚነሱባቸው ጉዳዮችን እየለዩ እየሰሩ መሆኑን የገለጹ ሲሆን፤ በጥርጣሬ ያሉ ጉዳዮችንም እየፈቱ እየሄዱ መሆኑን አንስተዋል።

አካታችነት በተለያዩ ደረጃዎች ሊገለጹ የሚችሉ ልዩነቶችንና ብዝኃነትን እንደሚያስተናግድ ይተነተናል። ሆኖም ግን አካታችነት በዕድሜ፣ በፆታ፣ በዘር፣ በሃይማኖት፣ በኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ወዘተ የተለዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች በአንድ ሂደት ውስጥ እንዲሳተፉ ከማድረግም ያለፈ ሰፊ ፅንሰ-ሐሳብ ይይዛል።

Post image

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምክክር ኮሚሽን 'ሁሉም አሸናፊ ይሆንበታል' ለሚለው ምክክር፣ ከታጣቂ ኃይሎች ጋር የመነጋገር ፍላጎት እንዳለው በተደጋጋሚ ቢገልጽም፤ ለዚህ ውይይት ግን ታጣቂዎች ነፍጥን ማስቀመጥ አለባቸው ብሏል። ምክክር በመጀመሪያ የሰላም መንፈስ እንደሚያስፈልገው የሚገልጸው ኮሚሽኑ፤ "ትጥቅን ወደ ጎን በማድረግ ለመግባባት ዝግጁ መሆን አስፈላጊ" መሆኑን ያስረዳል።

ለምክክሩ ውጤትም ታጣቂዎችን ጨምሮ የሁሉም አካላት ተሳትፎ ወሳኝ ነው የሚል እምነት አላቸው። ይሁን እንጂ ኮሚሽኑ በሚጠብቀው እና በሚጠበቅበት ልክ ታጣቂዎች ወደ ምክክሩ ሊመጡ አለመቻላቸው ከዕቅዳቸው ወደ ኋላ እንዲሉ አድርጓቸዋል።

በመሆኑም "ይህንን ለመፍታት ከመንግሥት ምን ይጠበቃል?" ለሚለው የአሐዱ ጥያቄ ምላሽ የሰጡት ኮሚሽነር አምባዬ ኡጋቶ፣ መንግሥት ኃላፊነት ስላለበት አስቻይ ሁኔታ እንዲፈጥር ጥያቄዎች ሲያቀርቡ መቆየታቸውን ተናግረዋል።

ታጣቂዎች ብቻ ሳይሆኑ የትግራይ ክልልም ወደ ምክክሩ እንዲመጣ ሁሉንም አካላት እያወያዩ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

ኮሚሽኑ ከሰሞኑ ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች እና ከሃይማኖት ተቋማት ጋር በነበረው የውይይት መድረክ ላይ ንግግር ካደረጉት ኮሚሽነሮች መካከል አምባሳደር መሐሙድ ድሪር ይገኙበታል።

Post image

ኮሚሽነሩ "ታጣቂዎች የሚያነሷቸው ጥያቄዎች በሕብረተሰቡ ተነስቷል" ያሉ ሲሆን፤ "ሊጎድል የሚችለው የእነሱ ተሳትፎ ብቻ ነው" ብለዋል። የታጠቁ ወገኖች በባሕርያቸው በብሔራዊ ምክክር ላይ አይሳተፉም ሲሉም፤ "መተማመን ጉድለቶች አሉ" ሲሉ አብራርተዋል።

የብሔራዊ ምክክር ኮሚሽን ትግራይም ሆነ ታጣቂዎች ሳይሳተፉ ምክክሩ ይደረጋል ወይም አይደረግም የሚል ውሳኔ ላይ አለመድረሱን ኮሚሽነር አምባዬ ተናግረዋል።

የብሔራዊ ምክክር ኮሚሽን የቀረው የቆይታ ጊዜ አጭር ቢሆንም፣ በቀረው ጊዜ ሂደት ውስጥ ዋናውን ጉባኤ አድርጎ ስራውን ማጠናቀቅ እንደማይችል መዘገባችን ይታወሳል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ