ጥቅምት 24/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) የንግዱ ዘርፍ ላይ የተሰማሩ የማኅበረሰብ ክፍሎች በተደጋጋሚ የሚያቀርቡትን የግብር ክፍያ ቅሬታ እንዲሁም በግብር ከፋዩ እና በገቢዎች ሠራተኞች መካከል የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን የሚፈታ ካውንስል መቋቋሙን የንግድ እና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት አስታወቀ።
ከሐይማኖት አባቶች፣ ከንግድ ቢሮ፣ ከገቢዎች ቢሮ እና ከጸጥታ አካላት የተውጣጡ አባላትን ያቀፈው ምክር ቤቱ፤ ችግሮች በቀላሉ እና በፍጥነት እልባት እንዲያገኙ በማድረግ የንግዱን ማኅበረሰብ ከመንግሥት አሰራር ጋር ለማቀራረብ ይሰራል ተብሏል።
የምክር ቤቱ ፕሬዝዳንት ወ/ሮ ዘሃራ መሐመድ፤ "የተተመነብኝ ግብር ከሰራሁት እና መክፈል ከሚገባኝ በላይ ነው" የሚል ተደጋጋሚ ቅሬታ በነጋዴው በኩል እንደሚነሳና ካውንስሉ ይህንን ችግር ለመፍታት እንደሚሰራ ለአሐዱ ተናግረዋል።
ፕሬዝዳንቷ በተጨማሪም፤ "ከግብር ክፍያ መብዛት በተጨማሪ በሒሳብ ኦዲት እና በተለያዩ የአሰራር ጉዳዮች ላይ ከፈጻሚዎች ጋር የሚፈጠርን አለመግባባት በተናጠል ለመፍታት ከመጣር ይልቅ በካውንስሉ በኩል ምላሽ የሚያገኝበትን አሰራር መዘርጋት መንግሥትም የሚገባውን ክፍያ እንዳያጣ እንዲሁም ነጋዴውም እንዳይጉላላ የሚያደርግ የመፍትሔ ሐሳብ ነው" ብለዋል።
የካውንስሉ የሥራ ዘመን 2 ዓመት ሲሆን ለተጨማሪ አንድ ዓመት ሊራዘም እንደሚችል የገለጹት ፕሬዝዳንቷ፤ 50 መቀመጫዎች እንዲሁም 7 የሥራ አስፈጻሚ እና የተለያዩ ኮሚቴዎች እንዳሉት አስታውቀዋል፡፡
ካውንስሉ እንዲቋቋም ያደረገው ምክር ቤት በቀጣይ ከገቢዎች ቢሮ ጋር በወር አንድ ጊዜ እየተገናኘ በነጋዴው በኩል የተነሱ ችግሮች መፍትሔ እንዲያገኙ ይሰራል፤ አፈጻጸሙንም ይከታተላል ተብሏል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
የግብር ይግባኝ አቤቱታዎችን እና የአሰራር ጥሰት ውዝግቦችን የሚፈታ የምክክር ካውንስል ተቋቋመ