ጥቅምት 24/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ)፣ የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ፓርቲ (ኢህአፓ)፣ እናት ፓርቲ፣ አንድ ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አኢዴፓ) እና የአማራ ግዮናዊ ንቅናቄ (አግን) በሚል ስያሜያቸው የሚታወቁ 5 ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የመሰረቱት "ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት" የተሰኘው "ጥምረት" ወደ "ውህደት" ሊያመራ እንደሚችል ፍንጭ ተሰጥቷል።

የውህደት እድሉ እንደሚኖር የተገለጸው የጥምረቱ አባል ፓርቲዎች ባላቸው ተቀራራቢ የፖለቲካ ፕሮግራም ምክንያት ነው ተብሏል።

የእናት ፓርቲ የአደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ አሰፋ አዳነ (ዶ/ር) በውህደቱ ዙሪያ ከአሐዱ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምልሽ ሲሰጡ፤ "በኢትዮጵያ የሚገኙ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተቀራራቢ ሐሳብ የሚያራምዱ ከሆነ ከተናጠል ትግል ይልቅ የጋራ ትግል ለግባቸው የበለጠ ያቀርባቸዋል" ብለዋል።

ጠንካራ አንድነት ፈጥሮ ለምርጫ መቅረብ የተሻለ አማራጭ እንደሆነ ያነሱት ዶክተር አሰፋ፤ "ከጥምረት ይልቅ ውህደት የበለጠ አዋጭ ነው" የሚል ሐሳብ አላቸው።

አሁን ያለው የሀገሪቱም ሆነ የተፎካካሪ ፓርቲዎች ሁኔታ "ፈታኝ" የሚባል ቢሆንም፤ የጥምረቱ አባል የሆኑት 5 የፖለቲካ ፓርቲዎች የመዋሀድ እድላቸው ከፍ ያለ ስለመሆኑ ለአሐዱ ተናግረዋል።

በተጨማሪም "ለፓርቲዎች ውህደት እንደ እንቅፋት ከሚታዩ ጉዳዮች መካከል የስልጣን ፍላጎት፣ የጠራ የፖለቲካ ርዕዮት አለመኖር፣ አለመተማመን እንዲሁም የገዢ ፓርቲዎች ጣልቃ ገብነት ይገኙበታል" ብለዋል።

ፖለቲካ ፓርቲዎች ከጥምረት ይልቅ ውህደት ላይ መስራት አለባቸው የሚለውን ሐሳብ የሚደግፉት ሌላው ፖለቲከኛ ጌትዬ ትርፌ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ "በ1997 ዓ.ም. በተካሄደው 3ኛው ሀገራዊ ምርጫ ለመወዳደር በፓርቲዎች የተመሰረተው "ቅንጅት" የፖለቲካ መነቃቃት መፍጠሩ ቢያስመሰግነውም ሕዝብ የሚፈልገውን ለውጥ ማምጣት አለመቻሉ 'ደካማ ጎኑ' እንደነበር አስታውሰዋል።

የ7ኛውን ሀገራዊ ምርጫ መቃረብ ተከትሎ 5 የፖለቲካ ፓርቲዎችን ካቀፈው "ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት" ቀደም ብሎ "መድረክ" የሚል መጠሪያ ያለው የፓርቲዎች ቅንጅት መፈጠሩ ይታወቃል።

መድረክ በተሰኘው ቅንጅት ከተካተቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል፤ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) እና አረና ትግራይ ለዲሞክራሲና ሉአላዊነት ይገኙበታል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ