ጥቅምት 24/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) በሰሜኑ ጦርነት በዝርፊያ እና በመሬት መንቀጥቀጥ ምክንያት ከፍተኛ ጉዳት እንደረሰበት የተገለጸውና 375 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው፤ የ"አዋሽ-ወልድያ-ሐራ ገበያ" የምድር ባቡር መስመር የጥገና ሥራ በተያዘው በጀት ዓመት እንደሚከናወን የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን አስታውቋል።
ኢትዮጵያን ከጅቡቲ ወደብ ጋር ለማገናኘት ታስቦ ከ10 ዓመታት በፊት በአንድ ነጥብ ሰባት ቢልዮን ዶላር በጀት ወደ ሥራ የገባው የምድር ባቡር መስመር ግንባታ፤ በጦርነቱ ከመጎዳቱ በፊት በግንባታ በሂደት ላይ እንደነበር የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጅነር ህሊና በላቸው አስታውሰዋል።
አክለውም፤ "ከመጠናቀቁ በፊት የተቋረጠውን የባቡር ሐዲድ የግንባታ ሂደት ለማስቀጠል እንዲቻል አስፈላጊ የቅድመ ግንባታ ጥናት ሥራዎች ተከናውነዋል፤ ስለዚህም በ2018 በጀት ዓመት የተቋረጠ ሥራቸው ዳግም ከሚጀመር ግዙፍ ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ ነው" ሲሉ ለአሐዱ ተናግረዋል።
ሥራ አስፈጻሚዋ "ወደ ጥገና እና ግንባታ ሥራ የምንገባበትን ሁኔታ አመቻችተናል" ይበሉ እንጂ፤ የፕሮጀክቱ ዳግም ግንባታ የሚጀመርበትን ትክክለኛ ቀን፣ የተመደበለትን በጀት እና የውድመቱን መጠን አልጠቀሱም።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
በጦርነት ጉዳት የደረሰበት የ"አዋሽ-ወልድያ-ሐራ ገበያ" የምድር ባቡር መስመር ዝርጋታ ሥራ በያዝነው ዓመት ይጀመራል ተባለ