መስከረም 27/2018 (አሐዱ ሬዲዮ)በአንድ ሕንጻ ላይ አንድ ቆጣሪ ብቻ በመኖሩ ምክንያት የመብራት መቆራረጥ ችግር እንዳስመረራቸውና ለተለያዩ ችግሮች እየተጋለጡ መሆኑን፤ የኮዬ ፈጬ ኮንዶሚኒየም ነዋሪዎች ለአሐዱ ቅሬታ አቅርበዋል።
ነዋሪዎቹ "ለአንድ ሕንጻ ላይ አንድ ቆጣሪ ብቻ መገጠሙ ለሁሉም ሰው ተጠቃሚ ለማድረግ ስለማይችል፤ የሃይል መቆራረጥ ችግር እርስ በእርስም እንድንጣላና ግጭት ውስጥ እንድንገባ እያደረገን ነው" ሲሉ ተናግረዋል።
እንዲሁም በአግባቡ ሳይጠቀሙ የመብራት አገልግሎት ክፍያ ከአቅማቸው በላይ እየከፈሉ መሆኑን የገለጹ ሲሆን፤ በከፈሉት ልክ እየተጠቀሙ እንዳልሆነም ተናግረዋል።
በዚህም በእጅጉን እንደተማረሩና በከፍተኛ ችግር ላይ እንደሚገኙ የተናገሩት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፤ በዚህ ችግር ውስጥ የሚገኙ ነዋሪዎች በአንድ ብሎክ ብቻ ከ50 በላይ መሆናቸውን ለአሐዱ ገልጸዋል።
እንዲሁም መብራት ቢቋረጥም ቶሎ የሚያስተካክል ባለሙያ እየደረሰላቸው እንዳልሆነ አያይዘው ተናግረዋል።

አሐዱም ጉዳዩን በተመለከተ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ አንዋር አብራርን አነጋግሯል።
በምላሻቸውም በአዲስ አበባና ዙሪያው የሚገኙ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ለአብዛኞቹ የቆጣሪ ቅየራ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
የሚቀሩት ለቆጣሪው የሚሆን መሠረታዊ ነገር ያላሟሉ እና ክፍያ ያልፈጸሙ ናቸው ብሏል።
በአጠቃላይ በኮንዶሚንየም ቤቶች ላይ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተደራሽን ለማረጋገጥ እየተሰራ እንደሚገኝም ገልጸዋል።
የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተደራሽነትን በማረጋገጥ ተገልጋዩ ማህበረሰብ በከፈለው ልክ ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚገባም ተመላክቷል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ