መስከረም 27/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) በጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ሻቻ ጎዝዲ ቀበሌ ሐምሌ 15 ቀን 2016 ዓ.ም በተከሰተው አስከፊ የመሬት መንሸራተት አደጋ ሰለባ ለሆኑ ዜጎች የተሰበሰበ፤ ከ60 ሚሊየን ብር በላይ ከዞኑ አደጋ ስጋት አካውንት ለመዝረፍ የሞከሩ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የዞኑ መንግሥት ኮሙኒኬሽን አስታውቋል፡፡

Post image

በዞኑ በተከሰተው የመሬት መንሸራተት አደጋ ምክንያት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሕይወታቸው ማለፉ የሚታወስ ሲሆን፤ በዚህ ምክንያት ከሀገር ውስጥና ከሀገር ውጭ ያሉ ግለሰቦች እንዲሁም፤ የተለያዩ አካላትና መንግሥታት የጉዳቱ ሰለባ ለሆኑ ዜጎች በዓይነትና በገንዘብ ድጋፍ ማድረጋቸው ይታወቃል፡፡

ይህም ድጋፍ ለተጎጂዎች በአግባቡ እንዲደርሳቸው የዞኑ መንግሥት ተፈፃሚነቱን በቅርበት እየተከታተለ መቆየቱን ገልጿል፡፡

ይህም የድጋፍ ገንዘብ በዞኑ አደጋ ስጋት አካውንት ተቀማጭ ተደርጎ የነበረ ሲሆን፤ በዚህም አካውንት ላይ የተፈጠረውን የወንጀል ሙከራ ሥራ በተመለከተ የዞኑ መንግሥት ኮሙኒኬሽን መግለጫ አውጥቷል፡፡

በመግለጫውም "..የሀገር ወስጥና የዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ለተጎጅ ሕብረሰብ ክፈሎች የለገሱትን ድጋፍ 'ወደ ኪሳችን ገብቶ ካልበለፀግን' በሚል አሰተሳሰብ የተጠመዱ አካላት ይህንን አስነዋሪና ስብዕና የጎደለውን ተግባር ለመፈፀም የወጠኑት ውጥን አልተሳካም" ብሏል፡፡

እነዚህም ግለሰቦች በአደጋው ለተጎዱ የሕብረተሰብ ክፍሎች ከመጣው ገንዘብ ላይ 60 ሚሊየን 276 ሺሕ 383 ብር ቀደም ሲል ተሠርቶ፤ ቮይድ በተደረገ ቼክ ቁጥር 42221123 አሰመስለው በማሳተም፤ ገንዘቡን ለመዝረፍ ሙከራ ማድረጋቸውን አስታውቋል።

ነገር ግን ከአዲስ አበባ ንግድ ባንክ ሸገር ቅርንጫፍ ለጎፋ ዞን አስተዳደር በተደረገ ጥቆማ መሠረት፤ ከአዲስ አበባና ክልል ፖሊስ ጋር በመተባበር ገንዘቡ ሳይወጣ ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ተገልጿል።

Post image

ሆኖም ግን በተለያዩ ሚድያዎች ለህብረተሰቡ ትክክለኛና ተጨባጭ መረጃ ከመስጠት ይልቅ የሚያወዛግብ መረጃ የሚያሰተላልፉ ሐሰተኛ ማበራዊ ሚዲያዎች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ የዞኑ መንግሥት ኮሙኒኬሽን አሳስቧል፡፡

ሕብረተሰቡ ከመንግሥት ትክክለኛ መረጃ ምንጭ የሚተላለፈውን መረጃ ብቻ እንደከታተልና ከሌሎች አወዛጋቢ መረጃ ምንጮች ራሳችውን እንዲቆጥቡ ያሳሰበም ሲሆን፤ "ቀጣይ የምርመራው ሂደት ሲጣራ የምናሳውቅ ይሆናል" ብሏል፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ