ጥቅምት 28/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) ኢትዮጵያ በድንበር አካባቢዎች የሚካሔደውን ሕገ-ወጥ የቁም እንስሳት ንግድ በመግታት ሀገሪቱ ከዘርፉ የምታገኘውን የውጭ ምንዛሪ ገቢ ለማሳደግ የገበያ ማዕከላትን በማቋቋም ወደ ሕጋዊ የንግድ ሥርዓት ለማስገባት እየሰራች መሆኑን ግብርና ሚኒስቴር አስታውቋል።
በሚኒስቴሩ የእንስሳትና ዓሳ ሀብት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አማካሪ አቶ ግርማ ሙሉጌታ እንደገለጹት፤ በድንበር አካባቢ ያለው የቁም እንስሳት ንግድ ሥርዓት ሕገ-ወጥ መሆኑ ሀገር ከዘርፉ ልታገኘው የምትችለውን ገቢ በእጅጉ እያሳጣ ነው።
ይህ ደግሞ በድንበር አካባቢዎች መደበኛ የገበያ ማዕከላት ባለመኖራቸው የተፈጠረ ችግር እንደነበር አንስተው፤ አርብቶ አደሩ ዋነኛው የገቢ ምንጩ እንስሳት በመሆናቸው፣ ተደራሽና ሕጋዊ ገበያ ሲያጣ ወደ ሕገ-ወጥ ግብይት እንደሚያመራ ተናግረዋል።

የአርብቶ አደሩ ዋነኛው የገቢ ሀብቱ እንስሳት መሆኑን የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታ አማካሪው፤ በአካባቢው ላይ መደበኛ የገበያ ማዕከላት ባለመኖራቸው ምክንያት በድንበር አከባቢ በሕገ-ወጥ መንገድ የቁም እንስሳት ግብይት እንደነበር ገልጸዋል።
አቶ ግርማ አክለውም፣ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በድንበር አካባቢዎች የገበያ ማዕከላት በመቋቋማቸው የቁም እንስሳት የንግድ ሥርዓት ወደ ሕጋዊ መስመር እንዲገባ ለማድረግ ጥረት መደረጉን ለአሐዱ ሬዲዮ ተናግረዋል።
ሆኖም እነዚህ የገበያ ማዕከላት በአግባቡ ተመርተው ወደ ሥራ በማስገባት ረገድ ክፍተት በመፈጠሩ፤ አሁንም አርብቶ አደሩ ወደ ሕገ-ወጥ ንግድ የማዘንበል ሁኔታ መኖሩን ጠቁመዋል።

የገበያ ማዕከሉ ተደራሽ ያለመሆኑና በአግባቡ አለመጠቀም በግልጽ የሚታይ ክፍተት እንደነበርም አስታውሰዋል።
የሕገወጥ ንግዱን ሙሉ በሙሉ በማስቀረት በሕጋዊ ግብይቱ የሚገኘው ገቢ የተሻለ እንዲሆን በማስቻል እየተሰራ ነው ብለዋል።
ለዚህም ምሳሌ የሚሆኑ የእንስሳት ማቆያዎችን በሚሌ እና በሌሎችም አካባቢዎች በመገንባት የተሻለ ለውጥ ማምጣት መቻላቸውን ነው ለአሐዱ የገለጹት።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በጉዳዩ ላይ የተደረገ ጥናት እንደሚጠቁመው፤ ኢትዮጵያ በምሥራቃዊ ድንበሯ በሚካሔደው መደበኛ ባልሆነ የቁም እንስሳት ንግድ ምክንያት በየዓመቱ ከ250 እስከ 300 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ልታገኘው የምትችለውን ገቢ እያጣች ነው።
የኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ከፍተኛ ተመራማሪ ራህማ ሙሰማ ባቀረቡት በዚህ ጥናት፤ በምሥራቃዊው ድንበር የሚካሔደው ሕገ-ወጥ የቁም እንስሳት ንግድ ድርሻ 86 በመቶ ያህል ይደርሳል።
ተመራማሪዋ እንዳስረዱት፤ ውስን የቴክኒክ ድጋፍ፣ ጥራት ያለው አገልግሎት አለመስጠት፣ ዘመናዊ ቁጥጥር ማነስ እና በድንበር ኬላዎች መሠረተ ልማት አለመኖር ለዚህ ሕገወጥ ንግድ መስፋፋት አስተዋፅዖ አድርገዋል።
በግብርና ሚኒስቴር የእንስሳትና ዓሳ ሀብት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አማካሪ አቶ ግርማ ሙሉጌታ፤ ችግሩን ለመቅረፍ በመሠረተ ልማት ግንባታ እና የገቢ ተጠቃሚነትን በማረጋገጥ እየተሠራ መሆኑን ማረጋገጫ ሰጥተዋል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ