ጥቅምት 28/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት በሚቀጥሉት 20 ቀናት ውስጥ፤ አዲሱን የኢ-ፓስፖርት አገልግሎት ሙሉ በሙሉ እንደሚጀምር ለአሐዱ ሬዲዮ አስታውቋል።

አገልግሎቱ "ከውጭ ታትሞ የሚመጣው የፓስፖርት ወረቀት የውጭ ምንዛሬው ውድ ከመሆኑም በላይ የሚፈጠሩ መጉላላቶች እንዲበዙ አድርጓል" በሚል፤ በሀገር ውስጥ የፓስፖርት ህትመትን ለመጀመር ዝግጅቱን አጠናቆ ወደ ሙከራ ህትመት መግባቱ ይታወሳል፡፡

በሙከራ ህትመቱ የሲስተም ፍተሻዎችን ማድረጉን የገለጸው ተቋሙ፤ አዳዲስ ቅርንጫፎችን የመክፍት እና የበፊቱ ፓስፖትር ሲሰጥ በነበረበት ሰዓት ቀጠሮ የተሰጣቸውን ዜጎች የማስተናገዱ ሥራ እየተጠናቀቀ መሆኑን አስታውቋል፡፡

Post image

የአገልግሎት መስሪያ ቤቱ የፓስፖርት አገልግሎት ዳይሬክተር አቶ ሙሉጌታ ታደሰ፤ ከዚህ በፊት በነበረው አሰራር ቀጠሮ የተሰጣቸውን ዜጎች ፓስፖርታቸውን እንዲወስዱ እየተደረገ መሆኑን ገለጸዋል

ይህ ሥራ ከ15 እስከ 20 ባሉት ቀናት ተጠናቆ፤ አዲሱ የፓስፖርት ስርዓት ወይም የኢ-ፓስፖርት አገልግሎት ወደ ሥራ እንደሚገባ ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡

በፓስፖርት አሰጣጥ ስርዓቱ ላይ የተለያዩ ሕገ-ወጥ ሥራዎችን ሲሰሩ የተገኙ አካላት እርምጃ እንደተወሰደባቸው አንስተው፤ 96 የውጭ ሀገር ዜጎች ፓስፖርት ለማውጣት ሲሉ ተይዘው ለሕግ አካላት ተላልፈው መሰጠታቸውን ገልጸዋል፡፡

በሠራተኞች በኩል ደግሞ 4 የተቋሙ ሠራተኞች ላይ አስተዳደራዊ እርምጃ እንደተወሰደም አስረድተዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ 4 ሚሊየን ፓስፖርት ለመስጠት መታሰቡን የገለጹት አቶ ሙሉጌታ፤ እስካሁን ባለው ጊዜ 630 ሺሕ ፓስፖርት መስጠት መቻሉን አስታውቀዋል፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ